በሪጅኑ ያለውን የኃይል አቅርቦት አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማዕከላዊ 1 ሪጂን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ወ/ማርያም እንዳስታወቁት በሪጂኑ በሚገኙት በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የኃይል ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡
የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት የማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም የማሳደግና የማሻሻል እንዲሁም የመቆጣጠሪያ ብሬከሮችን የማዘመን ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በለገጣፎ ማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያለው ትራንስፎርመር የመትከል እንዲሁም በአዲስ ኖርዝ ማከፋፈያ ጣቢያ ደግሞ የማሻሻያ ሥራዎች መጀመራቸውን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ ወንድወሰን ገለፃ በቦሌ ለሚ ማከፋፈያ ጣቢያ እና በለገጣፎ ማከፋፈያ ጣቢያ የኃይል ጭነት ሊያግዝ የሚችል የአቅም ማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በደብረ ብርሀን አንድ ማከፋፈያ ጣቢያ የተጀመረው የማሻሻያ ሥራ በአሁኑ ወቅት ከ50 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
የደብረ ብርሃን አንድ የማከፋፈያ ጣቢያ የ33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመር የብሬከር ቅየራ ሥራ መጠናቀቁን እና የ15 ኪሎ ቮልት ደግሞ እየተከናወነ መሆኑን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡
የገፈርሳ፣ ሆርማት፣ ቤላ እና ሙገር ማከፋፈያ ጣቢያዎችን የማሻሻያ ሥራ በቀጣዩ የበጀት ዓመት ለማከናወን መታቀዱንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
ሪጂኑ ከሚያስተዳድራቸው 22 ማከፋፈያ ጣቢያዎች መካከል የአዲስ ኖርዝ፣ ቤላ፣ ለገጣፎ፣ ደብረ ብርሃን አንድ፣ ወረገኑ እና ሱሉልታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የኃይል ጭነታቸው በአማካይ 80 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል።
በጣቢያዎቹ ላይ የአቅም ማሳደግ ሥራ ለማከናወን የሲቪል ሥራ ዲዛይንና የዋጋ ግምትን ጨምሮ ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
የማዕከላዊ 1 ሪጂን መሀል አዲስ አበባን ጨምሮ ከአዲስ አበባ በምዕራብ እስከ ሙገር፣ በሰሜን እስከ ገብረ ጉራቻ እንዲሁም በምስራቅ እስከ ደብረ ብርሃን ያሉ አካባቢዎችን ይሸፍናል፡፡

