የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሠራተኞችና የሥራ መሪዎችን አቅም የሚያጎለብቱ ሥልጠናዎች መስጠቱን በተቋሙ የሰው ኃይል ዘርፍ የሰው ሀብት ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ዳይሬክተር ወንድወሰን ካሳ(ዶ/ር) እንዳስታወቁት በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ በተመረጡ የሙያ መስኮች ላይ በውስጥ አቅምና በሦስተኛ ወገን የሠራተኛውንና የአመራሩን አቅም የሚገነቡ ከ64 በላይ ርዕሶች ላይ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
በሥልጠናዎቹ ከሦስት ሺህ በላይ ሠራተኞችና የሥራ መሪዎች ተሳታፊ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ ስልጠናው የተለያዩ የሥራ ክፍሎችን ታሳቢ ተደርጎ መሰጠቱንም ተናግረዋል።
መሰል ስልጠናዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመስጠት እስከአሁን የተሰጡት ስልጠናዎች ያስገኙትን ፋይዳ በጥናት ለመገምገም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ዶ/ር ወንድወሰን ገልፀዋል።
ጥናቱን በተያዘው በጀት ዓመት በማጠናቀቅ ለቀጣይ የአቅም ግንባታ ስራዎች እንደግብዓት ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም በኃይል ማመንጫ እና በኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፎች ላይ 40 የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሰልጣኞች በተቋሙ የሥልጠና ማዕከል የሚሰጠውን ስልጠና አጠናቀው በተለያዩ የኦፕሬሽን ዘርፎች መመደባቸውንም አብራርተዋል።
በሁለተኛ ዙር የሚሰለጥኑ 63 ሰልጣኞችን ለመቀበል ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሰው ሀብት ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ከአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር መፈራረሙን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”