በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 491 ነጥብ 17 ጊጋ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ ማመንጨቱን የጣቢያው ኃላፊ አስታወቁ።
ኃላፊው አቶ ታፈረ ሞገስ እንደገለፁት ጣቢያው በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለማመንጨት ካቀደው 577 ነጥብ 60 ጊጋ ዋት ሰዓት ውስጥ 491 ነጥብ 17 ጊጋ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ በማመንጨት የዕቅዱን 85 ነጥብ 04 በመቶ አሳክቷል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ ጣቢያው በዕቅዱ መስረት ያላመረተበት ምክንያት ግድቡ ከመጠን በላይ ውሃ አጠራቅሞ በመቆየቱ ውሃውን ለመልቀቅ፣ ለብዙ ዓመታት ተከማችቶ የቆየውን አፈርና ድንጋይ ለማውጣት እና በወንዙ ተፋሰስ ከ700 ሜትር-ኪዩብ በላይ የውሃ መሄጃ ቁፋሮ ለመስራት በርከት ያለ ጊዜ በመውሰዱ ነው።
በተጨማሪም በተደጋገሚ በመቐለ መስመር በሚፈጠረው መቆራረጥ ተርባይን በሚወጣበት ግዜ በቮልቴጅ ምክንያት ለረጅም ሰዓታት ተርባይን ማስገባት ባለመቻሉ አፈጻጸሙ ዝቅ ማለቱን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ጣቢያው ካሉት አራት ተርባይኖች በሁለቱ ተርባይኖች ኃይል እያመረተ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ታፈረ በቀሪ ወራት በጥገና ላይ ያሉትን ቀሪ ሁለት ተርባይኖች ወደ ሥራ በማስገባት በበጀት ዓመቱ ለማመንጨት የተያዘውን ዓመታዊ ዕቅድ ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
እያንዳንደቸው 75 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችሉ አራት ተርባይኖች ያሉት የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 300 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው።

