የኃይል መቆራረጥን በዘላቂነት ለመቅረፍ በቅንጅት እየተሰራ ነው

የኃይል መቆራረጥን በዘላቂነት ለመቅረፍ በቅንጅት እየተሰራ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ሪጅን ከትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽ/ቤት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የኃይል መቆራረጥን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን በሪጅኑ የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ገብረ እግዚአብሔር እንደገለጹት ሪጅኑ ሁለት ደንበኞች ያሉት ሲሆን እነሱም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ናቸው፡፡

ሁለቱ ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት ተያያዥነት ያለው በመሆኑ በከፍተኛ አመራሮቻቸው በኩል የጋራ መድረክ እንዳላቸው የገለጹት አቶ ሮቤል ሪጅኑ ባለው አቅም የሚሰጠው አገልግሎት የደንበኞቹን እርካታ የሚያሳድግና የህብረተሰቡን ፍላጎት ያማከለ እንዲሆን በጋራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ሮቤል ገለጻ በክልሉ ያለውን የኃይል መቆራረጥ በዘላቂነት በመቅረፍ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲኖር ተቋማቱ ያላቸውን የሰው ኃይል፣ ሀብትና ቁሳቁስ በማቀናጀት እና የጋራ መድረኮችን በመፍጠር እየሰሩ ነው፡፡

የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽ/ቤት ሥራ አሥፈጻሚ አቶ መስፍን ገብረ መድህን በበኩላቸው በክልሉ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በደረሰ ጉዳት እና የማሰራጫ መስመሮች ኔትወርክ በማርጀቱ የኃይል መቆራረጥ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

የኃይል መቆራረጡን በዘላቂነት ለመቅረፍና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ሪጅን ጋር በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የኃይል አቅርቦቱ ላይ ችግር ካጋጠመ ህብረተሰቡን በአግባቡ ማገልገል ስለማይቻል ተቋማቱ ያላቸውን ሀብት አቀናጅተው በመጠቀም የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Scroll to Top