ለጣቢያው ሠራተኞች ምቹ የሥራ ከባቢን ለመፍጠር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተከዜ የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ አስታወቀ፡፡
የጣቢያው የሰው ኃይል፣ ንብረትና ጠቅላላ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ መኮንን ገ/ሊባኖስ እንደተናገሩት የጣቢያው ሠራተኛ ምቹ የሥራ ከባቢ ተፈጥሮለት ሥራውን ተረጋግቶ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲያከናውን የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
ሠራተኛው አገልግሎት የሚያገኝበት እንዲሁም አቅሙን የሚያጎለብትበት የአሰራር ሥርዓት እየዘረጋን ነው የሚሉት ኃላፊው ለሠራተኛውና ለልጆቹ የሚሆን የመዋኛ ገንዳ፣ የዲ ኤስ ቲቪ አገልግሎት እና ሌሎች የመዝናኛ አማራጮችን መፈጠሩን ተናግረዋል።
ከወረዳው ትምህርት ቢሮ ጋር በመነጋገርና ፍቃድ በማውጣት የሠራተኛው ልጆች የሚማሩበት ከኬጂ እስከ 4ኛ ክፍል የሚያስተምር ትምህርት ቤት በጣቢያው ተከፍቶ በማስተማር ላይ መሆኑን አቶ መኮንን ገልጸዋል።
የትምህርት ቤቱን ጥራትና ደረጃ ለማሻሻል ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ ከ4ኛ ክፍል በላይ ለሆኑትና ሲቦኩ ከተማ ሄደው ለሚማሩት የሠራተኛው ልጆች በትምህርት መግቢያና መውጫ ሰዓት የሰርቪስ አገልግሎት በመሰጠት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ከኃይል ማመንጫ ቤት እስከ ሠራተኛ መኖሪያ ያለውን 9 ኪሎ ሜትር መንገድ የኮንክሪት አስፓልት ለማድረግ የሚያስችል ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
የጣቢያው ሠራተኞች ምቹ የሥራ ከባቢ ተፈጥሮላቸው ተረጋግተ ሥራቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲያከናውን የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ መኮንን አረጋግጠዋል።


