ሪጂኑ መስመሩን ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየሠራ ነው

ሪጂኑ መስመሩን ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየሠራ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡብ 2 ሪጂን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ የኢትዮ- ኬንያ ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት እንዳይደርስበት የቅድመ መከላከል ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ፋይበር ኦፕቲክስ ጥገና ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉብርሃን ሐዱሽ እንዳስታወቁት የተወሰኑ የመስመሩ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደሆኑ በተካሄዱ የፍተሻ ሥራዎች ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ምሰሶዎቹ በጎርፍ ከመጎዳታቸው በፊት መከላከል የሚያስችሉ የቅድመ መከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የማስተላለፊያ መስመሩ በሚያልፍበት የጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሼሌ መሌ ቀበሌ አካባቢ የጎርፍ ስጋት የተጋረጠበትን የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ከመውደቅ ለመከላከል የሚያስችል የአፈር መሸርሸር መከላከያና የጎርፍ ማስቀየሻ ግንብ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ ሙሉብርሃን ተናግረዋል፡፡

ምሰሶው ሲተከል ከወንዙ ከ35 ሜትር በላይ ርቀት የነበረው ቢሆንም በአካባቢው ከጥቅምት 2016 ዓ.ም ጀምሮ ባጋጠመ ከፍተኛ ጎርፍ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከወንዙ ያለው ርቀት ከ3 እስከ 4 ሜትር ብቻ እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡

በአካባቢው ያለው አፈር ልል በመሆኑ ችግሩ አሁን ካለበት ቦታ ላይ በፍጥነት ሊደርስ እንደቻለ ያነሱት ሥራ አስኪያጁ በአካባቢው ዝናብ ቶሎ ባለማቋረጡ ምክንያት ችግሩን በወቅቱ መቅረፍ አልተቻለም ብለዋል፡፡

መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ሥራ አስፈላጊው ጥናት እና ዲዛይን ተሰርቶለት በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን በሥራው ላይም 87 ሜትር ርዝመትና 5 ሜትር ቁመት ያለው የአፈር መከላከያ ግንብ ሥራ በሪጂኑ አቅም እየተከናወነ ይገኛል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ አሁን እየተከናወነ ካለው ሥራ በተጨማሪ በመስመሩ ላይ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ተጨማሪ አራት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች መለየታቸውን እና ችግሩ ሳይሰፋ ቀድሞ ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

Scroll to Top