የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የአርባ ምንጭ 2ኛ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ የሲቪል ግንባታ ሥራ 12 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን በፕሮጀክቱ የሳይት 1 ሥራ አስኪያጂ ገለጹ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ አንዱአለም መላኩ እንደተናገሩት የአርባ ምንጭ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ከወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ሺግዳን ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ኃይል ለመቀበልና ለመስጠት (LILO) ከሚዘረጋው መስመር ላይ በመቀጠል ኃይል ያገኛል፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያው ሁለት ባለ 125፣ ሁለት ባለ 63 እና ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር ትራንስፎርመሮች፤ አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ጥምር ገቢ መስመር እንዲሁም አንድ ባለ 132፣ 10 ባለ 33 እና 5 ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች እንደሚኖሩት አቶ አንዱአለም አስረድተዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የጣቢያው የመሬት ቁፋሮና ቆረጣ ሥራዎች የተጠናቀቁ ሲሆን የመሬት ሙሌት 69 በመቶ፣ የዲዛይን ሥራ 92 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች የማምረት ሥራ 58 በመቶ ተጠናቋል፡፡
የጣቢያው የመቆጣጠሪያ ክፍል እና የትራንስፎርመሮች ማስቀመጫ የመሰረት ቁፋሮ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ያነሱት ሥራ አስኪያጁ የታችኛው የመሰረት ኮንክሬት (pad) ሙሌት እና ብረት የማቆም ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
የግንባታ ሥራው ህዳር 2016 ዓ.ም የተጀመረው የአርባ ምንጭ ማከፋፈያ ጣቢያ አጠቃላይ የሲቪል ግንባታ ሥራ 12 ነጥብ 5 በመቶ ላይ መድረሱን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል ፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ለ50 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ጠቁመዋል።
ከ37 ነጥብ 09 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በጀት ተይዞለት እየተገነባ የሚገኘው የአርባ ምንጭ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ ሥራ ሲጠናቀቅ በአካባቢው ሊገነባ ለታቀደው የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና ለአካባቢው ማህበረሰብ አስተማማኝ እና በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡
የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት የአርባ ምንጭ ቁጥር 2፣ የሺግዳንና ቲርጋ የአዳዲስ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን፣ የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 እና አርባ ምንጭ ቁጥር 1 ማከፋፈያ ጣቢያዎችን የማስፋፊያ እንዲሁም የ424 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ሥራዎችን ያጠቃልላል፡፡
ከ178 ነጥብ 27 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በጀት ተይዞለት እየተከናወነ የሚገኘው የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት የግንባታ ሥራ ሀዮሰንግ ሄቪይ ኢንደስትሪስ ኮርፖሬሽን (Hyosung heavy industries corporation) በተሰኘ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን በማማከር ሥራው ላይ ደግሞ ባዩክሰን ፓወር (Byucksan power co.ltd) የተሰኘ ኩባንያ እየተሳተፈበት ይገኛል፡፡

