ጣቢያው በራስ አቅም ባከናወናቸው የጥገና ሥራዎች ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድኗል

ጣቢያው በራስ አቅም ባከናወናቸው የጥገና ሥራዎች ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድኗል

የጊቤ II የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በራስ አቅም በ3 የማመንጫ ዩኒቶች ውስጥ በሚገኙ የውሃ መቆጣጠሪያ ኖዝሎች ላይ ባከናወናቸው የጥገና ሥራዎች ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ሹመት በላቸው እንደገለፁት የኃይል ማመንጫው ካሉት 4 ዩኒቶች ውስጥ በ3ቱ ላይ የጥገና ሥራው ተከናውኗል።

ወደ ተርባይን የሚገባውን የውሃ መጠን ለመቆጣጠር በሚያገለግሉት ሹል ጫፎች ያላቸው የብረት ኖዝሌች በመበላታቸው በመዝጊያው በኩል ዘይት ማፍሰስ ጀምሮ እንደነበር ጠቁመዋል።

በ3ቱ የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች ውስጥ በሚገኙት የውሃ መቆጣጠሪያ ኖዝሎች ላይ በተከናወኑ የጥገና ሥራዎች የጣቢያውን የማመንጨት አቅም ዳግም ከፍ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

የውሃ መቆጣጠሪያ ኖዝሎቹ ተጠግነው ወደ ሥራ መግባታቸው ይስተዋል የነበረውን የውሃ አጠቃቀም ችግር ከመቅረፉ ባሻገር ዩኒቶቹ ወደ ሲስተም የሚገቡበትን ጊዜ ማሳጠሩን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ሹመት ገለፃ በአሁኑ ወቅት ጥገና የተከናወነላቸው 3ቱ ዩኒቶች በሙሉ አቅማቸው የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጩ ነው።

በቀረው አንድ ዩኒት ላይ ጥገና ለማከናወን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የኖዝል የጥገና ሥራው በውጭ ኩባንያዎች ቢከናወን ኖሮ ጉዳት የደረሰባቸውን ዕቃዎች ከመጠገን ይልቅ ወደ መቀየር ሊገባ ይችል እንደነበር የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ ይህም ተቋሙን ለተጨማሪ ወጪ ይዳርገው እንደነበር ገልፀዋል።

በኃይል ማመንጫ ጣቢያው ከጊዜ ወደ ጊዜ በራስ አቅም እየተከናወኑ የሚገኙ የጥገና ሥራዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን አቶ ሹመት አመልክተዋል።

በማመንጫ ጣቢያው አጠቃላይ የጥገና እና የኦፕሬሽን ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዙ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች መጀመራቸውንም ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል።

የዲጂታላይዜሽን ሥራዎቹ የጣቢያውን የጥገናና የኦፕሬሽን ሂደቶች በመከታተልና ያጋጠሙ ችግሮችን በፍጥነት በመለየት ለመፍታት የማይተካ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

Scroll to Top