የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ለቀጣናዊ የኃይል ትስስር አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ለቀጣናዊ የኃይል ትስስር አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር አስተማማኝ ኃይል እንዲያስተላልፍ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡብ 2 ሪጂን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የማስተላለፊያ መስመሮችና የፋይበር ኦፕቲክስ ጥገና ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉብርሃን ሐዱሽ እንዳስታወቁት የተጀመረውን ቀጣናዊ የኃይል ትስስር ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት ሪጂኑ ከሚያስተዳድራቸው ሌሎች መስመሮች በተለየ መልኩ ለኢትዮ-ኬንያ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር የቅርብ ክትትል ይደረግለታል፡፡

መስመሩ በሠው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ኃይል ማስተላለፍ እንዳያቋርጥ ለማድረግ ከመደበኛ የፍተሻና የጥገና ሥራዎች በተጨማሪ የድንገተኛ ፍተሻዎች እንደሚከናወኑም አስታውቀዋል፡፡

ለዚህም በመስመሩ ላይ ብቻ የፍተሻና የጥገና ሥራዎችን የሚያከናውን ቡድን ተዋቅሮ እየሰራ እንደሚገኝ ነው አቶ ሙሉብርሃን የተናገሩት፡፡

ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት በፍተሻ ሥራው ለጎርፍ አደጋና ለሥርቆት ተጋላጭ የሆኑ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ተለይተው የተለያዩ የቅድመ መከላከል ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ከቅድመ መከላከል ሥራዎች በተጨማሪ ስርቆት የተፈፀመባቸውን ምሶሶዎች በመከታተል የጥገና ሥራዎች በወቅቱ እየተከናወኑ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የፍተሻ ሥራዎቹ መስመሩ ኃይል ማስተላለፍ ከማቋረጡ በፊት የገጠሙትን ችግሮች በወቅቱ ለማስተካከል እንደሚያግዙ አቶ ሙሉብርሃን አንስተዋል፡፡

የኢትዮ – ኬንያ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር 1 ሺ 66 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይሸፍናል፡፡

Scroll to Top