በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአሸጎዳ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 28 ነጥብ 565 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨቱን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለጹ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ካህሰ ፀሐይ እንደገለፁት የኃይል ማመንጫ ጣቢያው በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 45 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማመንጨት አቅዶ የነበረ ቢሆንም ማሳካት የቻለው የዕቅዱን 63 ነጥብ 47 በመቶ ነው።
አፈጻጸሙ ከእቅዱ አንጻር ያነሰው ለረጅም ጊዜ ሥራ አቁመው የነበሩ ተርባይኖችን ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት በቂ የጥገና ባለሙያና መለዋወጫ ባለመኖሩ እንዲሁም ተርባይኖችች ለረጅም ጊዜ ሳይሰሩ በመቆየታቸው ምክንያት ተጨማሪ ቴክኒካል ችግር ይዘው በመገኘታቸው ነው ብለዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ጣቢያው ካሉት 84 ተርባይኖች አሁን ላይ 25 ተርባይነችን ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል።
ተቋሙ የመለዋወጫ ችግሩን ለመፍታት እና ኤ ኤፍ ዲ ከተባለ የፈረንሳይ ተቋም ጋር በመነጋገር ሙሉ ተርባይኖችን ወደ ሥራ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት ተጨማሪ ተርባይኖች ወደ ሥራ ስለሚገቡ የነበሩ እጥረቶችን በማረም የታቀደውን ዓመታዊ የኃይል ምርት ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
30 ባለ ሁለትና 54 ባለ ሶስት ክንፍ በድምሩ 84 ተርባይኖች ያሉት የአሸጎዳ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ 120 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው።

