ተቋሙ ከአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለው ስምምነት ተፈራርመ

ተቋሙ ከአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለው ስምምነት ተፈራርመ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ በከፍተኛና መካከለኛ አመራር ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ናቸው።

በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለጹት ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣትና በኃይል ዘርፍ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል አመራር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

የኃይል ዘርፉ ከፍተኛ የመሪነት አቅምን የሚጠይቅ በመሆኑ የመግባቢያ ስምምነቱ ብቁ አመራር በመፍጠር በአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን የያዝነውን እቅድ ከግብ በማድረስ በኩል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ተቋሙ የሀገር ውስጥ የኃይል ፍጆታን በመሸፈን የጎረቤት ሀገራትን በኃይል እያስተሳሰረ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በኃይል ዘርፉ ብቁ የሆነ የልህቀት ማዕከል ለመገንባት ተቋሙ የያዘውን ዕቅድ ወደ መሬት ለማውረድ የመግባቢያ ስምምነቱ እንደሚረዳ ገልፀዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱን ወደ መሬት በማውረድ በአጭር ጊዜ በኃይል ዘርፍ ለተሻለ ውጤት የሚተጋ አመራር እንደሚፈጥር እምነታቸው መሆኑን ኢንጂነር አሸብር ገልጸዋል።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ አካዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሀገራችን በኃይል ራሷን እንድትችል ከማድረግ ባሻገር ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ የውጭ ምንዛሬን እያስገነ ያለ ተቋም መሆኑን ጠቁመዋል።

የተቋማቱ ግንኙነት የቆየ ቢሆንም ባለፉት አራት ወራት ከሁለቱም ተቋማት የተውጣጣ ቡድን በጋራ ለመስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲያደረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም አሟጦ በመጠቀም ወደ ሀብት መቀየር የሚችል ብቁና ጠንካራ አመራሮችን ለማፍራት የሚረዳ መሆኑን የገለጹት አቶ ዛዲግ ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በአመራር ልማት፣ በአመራር ዕውቅና አሰጣጥና በሃሳብ ማበልጸጊያ ማዕከል ግንባታ ዙሪያ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

አካዳሚው የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ወደ ተግባር በመቀየር በዘርፉ ያለውን የአመራር አቅምን በቀጣይነት ለማሳደግ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top