የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ጠብቆ እንዲከናወን ተገቢው የቁጥጥርና ክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራዎች ቡድን መሪ አስታወቁ።
የቡድን መሪው አቶ እሸቱ ወርቁ እንደገለፁት የግድቡን የጥራት ደረጃ ለማስጠበቅ ዘመኑ ያፈራቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ የአሰራር ሥርዓቶች ተዘርግተው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።
የጥራት ደረጃውን ለማረጋገጥ የሚሰሩ የክትትል ሥራዎች በግንባታ ወቅት የሚፈጠሩ ጉድለቶችን ለመለየትና ለማረም እንደሆነም ነው ቡድን መሪው የገለፁት።
በአሁኑ ወቅት የግድቡን የግንባታ የጥራት ደረጃ ለማረጋገጥ ከሥራ ተቋራጩና ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም ነው የጠቀሱት።
በኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የኳሊቲ አሹራንስ ባለሙያ አቶ አረጋ ስለሺ እንደተናገሩት የጥራት ማረጋገጥ ሥራዎች የሚሰሩት ግድቡ በአማካይ ከ50 ዓመት በላይ ኃይል እያመነጨ እንዲቆይ ለማስቻል ነው።
በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ በተቀመጠለት የዲዛይንና የጥራት ማረጋገጫ መስፈርቶች መሰረት በከፍተኛ ርብርብ እየተገነባ እንደሆነም ነው አቶ አረጋ ያብራሩት።
በስታንቴክ ኢንተርናሽናል የማማከር ሥራዎች የኳሊቲ አሹራንስ ባለሙያ አቶ ታደሰ ሀብቴ በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ የተለያዩ የማማከርና የድጋፍ ሥራዎች እየተሰሩ ነው።
በግንባታ ወቅት ለሚፈጠሩ ችግሮች የመፍትሔ ሀሳቦችን በማቅረብ የማማከር ሥራዎች እንደሚሰሩም ነው ባለሙያው ያመለከቱት።
እንደ ባለሙያው ገለፃ የሥራ ተቋራጩ የግድቡን ግንባታ ለማስፈፀም ያስቀመጣቸውን የዲዛይንና መሰል መስፈርቶች በማሟላት እያከናወነ ስለመሆኑ ጥብቅ የፍተሻና የሱፐርቪዥን ሥራዎች ይሰራሉ።
ለግንባታ ሥራው በሚውሉ ግብዓቶች ላይ የላብራቶሪ ናሙና ምርመራዎች እንደሚደረጉ የጠቀሱት ባለሙያው ይህም የግድቡን የጥራት ደረጃ ለማረጋገጥ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

