በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አሰራሮችን ለማዘመን እየተተገበረ ያለው የሳፕ ሲስተም በተቋሙ ወጥ የሆነ የአሰራር ሥርዓት እንዲኖር ማድረጉን በተቋሙ የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡
የደቡብ 1 ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ንጉሴ እንደተናገሩት የሳፕ ሲስተም በሪጂኑ የሚከናወኑ የአስተዳደር፣ የፋይናንስና ተያያዥ ሥራዎች ወረቀት አልባ በሆነ አሰራር እንዲከወኑ በማድረግ ሥራዎችን ከማቀላጠፍ ባለፈ ተቋሙን ከተጨማሪ ወጪ እያዳነ ይገኛል፡፡
የምዕራብ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ በቀለ በበኩላቸው የሳፕ ሲስተም ሪጂኑ ከሌሎች የተቋሙ የሥራ ክፍሎች ጋር የሚኖረውን ግንኙነት እንዲጠናከር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
አሰራሩ ሪጅኑ በሥሩ ከሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ጋር የሚኖረውን የመረጃ ልውውጥ ለማቀላጠፍ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ኃይሉ ገለፃ የሳፕ ሲስተም ተግባራዊ ባይደረግ ኖሮ በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከተቋሙ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶች ሊቋረጡ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር፡፡
የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ውበት አቤ በበኩላቸው እየተተገበሩ ያሉ የአሠራር ማዘመን ሥራዎች ተቋሙን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እንደሚያግዙ ገልጸዋል፡፡
የአሰራር ሥርዓቱ በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ይስተጓጎል የነበረውን የመረጃ ልውውጥ ለማስቀጠል ከማስቻሉም ባለፈ የተጠያቂነት ሥርዓትን ለመዘርጋት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የማዕከላዊ 1 ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ወ/ማሪያም እንደገለጹት ደግሞ የአሰራር ሥርዓቱን ማዘመን ከሪጅኖች ወደ ዋናው መስሪያ ቤት የሚደረጉ ምልልሶችን በማስቀረት ሥራዎችን በተያዘላቸው መርሃ ግብር ለመፈጸም እያገዘ ይገኛል፡፡
እንደ ሪጅን ኃላፊዎቹ ገለፃ በመጀመሪያው ምዕራፍ ተግባራዊ የተደረጉ የሳፕ ሞጁሎች መረጃዎችን በአግባቡ አደራጅቶ ለመያዝ እና በተቋሙ ወጥና ተመሳሳይ የሆነ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት አስችለዋል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ የሚተገበረው “የፕላንት ሜንቴናንስ ሞጁል” ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ሲውል በሁሉም ሪጅኖች ወጥ የሆነ የኢንስፔክሽንና የጥገና የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
ሥርዓቱ የጥገና ሥራዎች የሚከናወኑበት እና የመለዋወጫ ዕቃዎች የሚገኙበት ሁኔታን በቀላሉ ለማወቅና ለመከታተል እንደሚረዳም አስታውቀዋል፡፡
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



