በኃይል ማመንጫ ጣቢያው የልምድና የዕውቀት ሽግግር ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ናቸው

በኃይል ማመንጫ ጣቢያው የልምድና የዕውቀት ሽግግር ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ናቸው

በጊቤ II የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የኦፕሬሽን እና የጥገና ዘርፎች ላይ የልምድ ልውውጥ እና የዕውቀት ሽግግር ሥራዎች በስፋት እየተሰሩ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለፁ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ሹመት በላቸው እንደገለፁት በጣቢያው እየተሰራባቸው የሚገኙ የልምድና የዕውቀት ሽግግር ሥራዎች ውጤታማ ሆነዋል።

የጣቢያውን ሠራተኞች በኦፕሬሽን እና ጥገና ሥራዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

አዳዲስ መሐንዲሶች እና የቴክኒክ ባለሙያዎች ከነባር የጣቢያው ሠራተኞች ጋር በቅንጅት እያከናወኗቸው የሚገኙ የጥገና እና የኦፕሬሽን ሥራዎች የጣቢያውን የመፈፀም አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻሉት መምጣታቸውን ሥራ አስኪያጁ አመልክተዋል።

ዘመኑ የደረሰባቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለጥገና እና ኦፕሬሽን ሥራዎች አመቺ ሁኔታ ፈጥረዋል ያሉት አቶ ሹመት በየጣቢያዎቹ የሚገኙትን መረጃዎች ማጥናትም ለልምድና የዕውቀት ሽግግሩ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

በጣቢያው የጥገና ባለሙያ የሆነችው ወ/ሪት መልካም ባወቀ እንዳለችው ጣቢያው በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ታውቃቸው የነበሩ ዕውቀቶችን ወደ ተግባር ለመለወጥ እንዳገዛት ተናግራለች።

በኃይል ማመንጫ ጣቢያው በቆየችበት አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በጥገና ሥራዎች ላይ በርካታ ልምዶችና ዕውቀቶችን እያገኘች መምጣቷንም ነው የገለፀችው።

የጣቢያው የጥገና ባለሙያ የሆነው አቶ ፋንታሁን እስከዚያ በበኩሉ በጣቢያው እየተከናወኑ የሚገኙ የጥገና ሥራዎች በቅንጅት የሚሰሩ መሆናቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንዳገዛቸው ተናግሯል።

ከጣቢያው ኃላፊዎችና ከተቋሙ የቴክኒክ ድጋፍ ክፍል የተለያዩ ሙያዊ እገዛዎች እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ነው አቶ ፋንታሁን ያመለከተው።

Scroll to Top