በሪጅኑ በተፈፀመ ሥርቆት ሁለት የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ወድቀዋል

በሪጅኑ በተፈፀመ ሥርቆት ሁለት የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ወድቀዋል

ከለገጣፎ – ቃሊቲ በተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈፀመ ስርቆት ሁለት የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች መውደቃቸውን የማዕከላዊ አንድ ሪጅን አስታወቀ፡፡

የሪጅኑ የማስተላለፊያ መስመርና ፋይበር ኦፕቲክስ ሥራ አስኪያጅ አቶ በሱፈቃድ በቀለ እንዳስታወቁት በመስመሩ ላይ ሚያዚያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ከሌሊቱ 6 ሰዓት አካባቢ በሁለት የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ ስርቆት ተፈፅሟል፡፡

መስመሩ ላይ የተፈፀመው ሥርቆት የግሪድ ሥርዓቱን በመረበሽ በለገጣፎና ቃሊቲ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የኃይል መቆራረጥ ማስከተሉን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

የወደቁ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎችን ጠግኖ ወደ ኦፕሬሽን ለማስገባት የአንድ ወር ጊዜ ያስፈልጋል ያሉት ሥራ አስኪያጁ በመስመሩ አማካኝነት ኃይል የሚያገኙ አካባቢዎች ኃይል ለማግኘት ወደ ፈረቃ ሊገቡ ይችላሉ ብለዋል፡፡

በሁለቱ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ የተፈፀመውን ሥርቆት መልሶ ለመተካት ኃይል በመቋረጡ የሚታጣውን የኤሌክትሪክ ምርት ሽያጭ ሳይጨምር ተቋሙ አስከ 5 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ኪሳራ እንደሚደርስበት ጠቅሰዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት 9 ወራት ውስጥ ሪጅኑ በሚያስተዳድራቸው መስመሮች ላይ ከ3 ሺህ 500 በላይ የታወር ብረቶች አካላት በሌቦች ተሰርቀዋል ያሉት አቶ በሱ ፈቃድ በዚህም በተቋሙ ላይ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ መድረሱን ገልፀዋል፡፡

የሪጅኑ የጥገና ባለሙያ አቶ ሰይድ አስማማው በበኩላቸው በአካባቢው የሚፈፀመው ተደጋጋሚ ሥርቆት መደበኛ የጥገና ሥራዎችን ከማስተጓጎሉም በላይ ተቋሙን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ከቃሊቲ – ለገጣፎ በሚያልፉ የኃይል ተሸካሚ ምሰሦዎች ላይ ስርቆቱ እጅግ የከፋ ነው ያሉት ባለሙያው አንድ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ እስከ 8 ጊዜ በሌቦች መሰረቁን ጠቅሰዋል፡፡

በኢ.ኤ.ኃ በማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የሪጅኖች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ እስማኤል ሙዘይን እንደገለፁት በአካባቢው የሚስተዋለውን ስርቆት ለማስቆም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡

ይሁን እንጂ የተደረጉት ውይይቶች ተጨባጭ ለውጥ አለማምጣታቸውን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የአካባቢው ማህበረሰብ በመሰረተ ልማቶቹ ላይ የእኔነት ስሜት አለማዳበሩ፣ የፀጥታ አካላት ክትትል ማነስ እና የህግ መላላት በአካባቢው ለሚታየው ስርቆት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡

ስለሆነም ማህበረሰቡ በአካባቢው የሚገኙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቅ እና የጸጥታ አካላትም ተጠርጣሪዎችን ወደ ህግ በማቅረብ አስተማሪ ቅጣት እንዲወሰድባቸው እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Scroll to Top