በደቡብ 1 ሪጂን የሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረቡ መሆኑን የሪጂኑ ዳይሬክተር ገለጹ።
የሪጂኑ የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ንጉሴ እንደገለጹት በሪጂኑ ከሚገኙ 12 ማከፋፈያ ጣቢያዎች 11ዱ ተጨማሪ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም አላቸው፡፡
በሪጂኑ የሚገኙ ሁሉም ማከፋፈያ ጣቢያዎች 1300 ሜጋ ዋት ኃይል የመጫን አቅም ያላቸው ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለደንበኞቹ እየቀረበ ያለው 567 ሜጋ ዋት እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ከዲላ ማከፋፈያ ጣቢያ በስተቀር ሌሎች ጣቢያዎች ተጨማሪ ደንበኞችን የማስተናገድና አስተማማኝ ኃይል የማቅረብ አቅም እንዳላቸውም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የዲላ ማከፋፈያ ጣቢያ በ15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመር ትራንስፎርመር ላይ የመጫን አቅሙ ሙሉ በሙሉ ስለሞላ በአሁኑ ወቅት ኃይል የሚፈልጉ ደንበኞች ከ33 ኪሎ ቮልት በጊዜያዊነት ኃይል እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በ15 ኪሎ ቮልት ላይ የኃይል ጥያቄው እየጨመረ በመምጣቱ ከደንበኞች የሚቀርቡ ተጨማሪ የኃይል ጥያቄዎችን ለመመለስ ጣቢያው የአቅም ማሳደግ ሥራ እንደሚያስፈልገው አቶ ምትኩ አስታውቀዋል፡፡
ሪጂኑ ከሚያካልላቸው አካባቢዎች መካከል ሀዋሳ፣ ዲላ፣ ሻሸመኔ እና ሻኪሶ ያለው የኃይል ፍላጎት በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ያነሱት ዳይሬክተሩ የኃይል ጥያቄውን በወቅቱ ለመመለስ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ተጨማሪ ብሬከር የመትከልና የማዘመን ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ምትኩ ገለፃ የሻሸመኔ፣ ሻኪሶ፣ ይርጋለም 1 እና ዲላ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ብሬከር የማዘመን ሥራ እየተሰራ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅትም የሻሻመኔ 33 ኪሎ ቮልት የብሬከር ቅየራ ሙሉ በሙሉ ጠናቀቁንና የሻኪሶ ደግሞ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የይርጋለም 1 እና የዲላ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የብሬከር የቅየራ ሥራ በጣቢያዎቹ ላይ ጊዜያዊ ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ ከተተከለ በኋላ እንደሚከናወን ገልጸው በአሁኑ ወቅትም ለባለሙያዎች ስልጠና የመስጠትና ለቅየራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ወደ ጣቢያዎቹ የማጓጓዝ ሥራዎች መከናወኑን አመልክተዋል፡፡
የደቡብ 1 ሪጂን የሲዳማ ክልልን ሙሉ በሙሉ፤ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ፣ ባሌ፣ ምስራቅ ባሌ፣ ቦረና፣ ምስራቅና ምዕራብ ጉጂ ዞኖችን እንዲሁም ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጌዲዮ ዞንን የሚያገለግል ነው፡፡
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


