የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታን በተያዘለት ጊዜ ገደብ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት የኮንትራት አስተዳደር ሥራዎች በአግባቡ እየተሰሩ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፕሮጀክቱ የኮንትራት አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ቡድን መሪ አቶ ኢዩኤል ሰለሞን እንደተናገሩት የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዩሮ ነው።
በአሰሪው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና በተቋራጩ ዊ ቢውልድ ወይም በቀድሞው ሳሊኒ መካከል ጥብቅ የሆነ የሥራ አካሄድ እንዲኖር ለማድረግ የክትትል ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የተቀመጡ ውሎችን አፈፃፀም የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራዎች በተገቢው መንገድ እየተከናወኑ መሆኑን አቶ ኢዩኤል ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ የኮንትራት አስተዳደር ክፍል በግድቡ ግንባታ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ሥራ ተቋራጮች ላከናወኗቸው ሥራዎች በየወሩ የሚጠይቋቸውን የፋይናንስ ጥያቄዎች በማጣራት ተፈፃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የፕሮጀክቱ የግንባታ ጠቅላላ ወጪ እንደ ሲቪል እና ኤሌክትሮሜካኒካል ሥራዎች ዓይነትና መጠን በብር እና በዩሮ የሚከፈሉ መሆናቸውን አቶ ኢዩኤል ገልፀዋል።
የፕሮጀክቱ አብዛኛው የሲቪል ሥራ ሀገር ውስጥ በሚገኙ ግብዓቶች እየተከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ቡድን መሪው በዚህም ምክንያት ክፍያዎች ተፈፃሚ እየተደረጉ የሚገኙት በብር እንደሆነም ነው ያመለከቱት።
እንደ አቶ ኢዩኤል ገለፃ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ከዲዛይን ጀምሮ እስከ ምርት ሂደትና ገጠማ ድረስ በዩሮ የሚከፈል በመሆኑ የሚያስችል የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል።
በኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የኮንትራት አስተዳደር ሂደት ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ ለመቅረፍ ከጊቤ-III የኃይል ማመንጫ ጣቢያ እና ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የተለያዩ ልምዶችና ዕውቀቶች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት እንዳይጓተት ለማድረግ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ኢዩኤል አረጋግጠዋል።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

