የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የላከው ቡድን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምስራቅ ሪጅን 2 በመገኘት የመስክ ጉብኝት አደረገ።
የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ አቶ እያሱ ሳላ እንደገለጹት የመስክ ምልከታው ዓላማ የቋሚ ኮሚቴው አባላት የሪጅኑን የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የሥራ እንቅስቃሴን በአካል ተገኝቶ በመጎብኘት ግብረ መልስ ለመስጠት ነው።
የሰሜን ምስራቅ ሪጅን 2 ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም የሪጅኑ አመራሮችና ሠራተኞች የአካባቢውን የአየር ንብረት ተቋቁመው ባደረጉት ጥረት በአጭር ጊዜ የተመዘገበው ውጤት አበረታች መሆኑን የቡድኑ አባላት አንስተዋል።
ሪጅኑ አገልግሎት አሰጣጡን የተቀላጠፈ ለማድረግ የራሱን ቢሮ መገንባትና የካይዘን አሠራርን በአግባቡ ሥራ ላይ ሊያውል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምስራቅ ሪጅን 2 ዳይሬክተር አቶ ሀሰን መሐመድ በበኩላቸው በሪጅኑ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሪጅኑ የሠራተኛ ፍልሰት በመኖሩ ሠራተኞች በሪጅኑ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ ለማድረግ ለሠራተኞች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር በተጨማሪ የአካባቢውን ወጣቶችን በማሰልጠን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሪጅኑ የሚፈጸመው የኤሌክትሪክ መሠረት ልማት ስርቆት በስራቸው ብሎም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ በርካታ ጉዳት እየደረሰ መሆኑም ተገልጿል።
ስለሆነም የአካባቢው መስተዳድር፣ ሕዝቡና የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ዘለቄታዊ እልባት ለመስጠት እንዲሰሩ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የቡድን አስተባባሪው የተከበሩ አቶ እያሱ ሳላ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት በሀገር ማህበረ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ ያለ ችግር በመሆኑ ችግሩ እንዲፈታ ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት የሚያቀርቡ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱም ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል ጠንከር ያለ ሕግ እንዲያወጣ ቋሚ ኮሚቴው ጥረት የሚያደርግ መሆኑን የጠቆሙት አስተባባሪው በሪጅኑ የሚታየውን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት ለመከላከል የአካባቢው መስተዳድር በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።
በሪጅኑ ለሥራ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከዋናው መ/ቤት፣ ክልሉ መንግስት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የተከበሩ አቶ እያሱ ጠቁመዋል።