ለትንሳዔ በዓል ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት በ25 በመቶ እድገት ያሳየ የኃይል አቅርቦት ዝግጁ ተደርጓል

ለትንሳዔ በዓል ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት በ25 በመቶ እድገት ያሳየ የኃይል አቅርቦት ዝግጁ ተደርጓል

ለትንሳኤ በዓል የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም ዝግጅት መደረጉን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የብሔራዊ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል አስታወቀ።

በማዕከሉ የሪል ታይም ኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት እንግዳ እንዳስታወቁት በዋዜማውና በበዓሉ ዕለት በመላው ሀገሪቱ የሚኖረው የኃይል ፍላጎት 3 ሺህ 497 ሜጋ ዋት ሊደርስ እንደሚችል ተተንብይዋል፡፡

በመሆነም ይህን ታሳቢ ያደረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሰራታቸውን እና ሊመጣ የሚችል ተጨማሪ የኃይል ፍላጎትን ለማስተናገድ 300 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመጠባበቂያነት ዝግጁ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ጉልላት ገለፃ በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ሁሉም ዩኒቶች ላይ የፍተሻ ሥራ በማከናወን ዩኒቶች ዝግጁ ተደርገዋል፡፡

የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለኃይል መቋረጥ ምክንያት እንዳይሆኑ የቅድመ መከላከልና የፍተሻ ሥራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አምና በተመሳሳይ ወቅት የኃይል ፍላጎቱ 2 ሺህ 850 ሜጋ ዋት ሊደርስ እንደሚችል ተተንብዮ ለዚያ የሚሆን ኃይል ዝግጁ መደረጉን እንዲሁም ተጨማሪ 350 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመጠባበቂያነት መያዙን አስታውሰዋል፡፡

ለዘንድሮ የትንሳዔ በዓል ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት በ25 በመቶ ዕድገት ያለው የኃይል አቅርቦት ዝግጁ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ በበዓሉ ወቅት የኃይል መቆራረጥ እንዳይከሰት ለማድረግ ከተቋሙ በቀጥታ ኃይል የሚያገኙ የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች እና ከፍተኛ ቮልቴጅ ተጠቃሚዎች ኃይልአጠቃቀማቸውን እንዲቀንሱ ተደርጓል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል ካሉ ደንበኞች መካከልም ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎችና ዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች ኃይል አጠቃቀማቸውን እንዲቀንሱ ከስምምነት ተደርሷል፡፡

ከበዓሉ ጋርተያይዞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት እና በሚሰራው ሥራ ላይ ውሳኔ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች መፍትሔ ለመስጠት በየደረጃው የሚገኙ የዘርፍ ኃላፊዎችና የብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል የሥራ ኃላፊዎች በኦፕሬሽን ሥራው ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

Scroll to Top