በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጅነሪንግ ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ባለፉት አምስት ዓመታት በተገኙ መልካም ተሞክሮዎች እና ተግዳሮቶች እንዲሁም በ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ላይ ወይይት አካሄዱ።
የዘርፉ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ውድነህ የማነ እንደገለፁት ባለፉት አምስት ዓመታት እንደዘርፍ በርካታ ውጤቶችና መልካም ተሞክሮዎች ተገኝተዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን ለአፈፃፀም ክፍተት የሆኑ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውንም ጠቁመዋል።
የውይይይ መድረኩ ዘርፉ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ከሠራተኞች በቂ ግብዓት ለመሠብሰብና በተደጋጋሚ ለሚያጋጠሙ ተግዳሮቶች ዘላቂ የጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ እንደተዘጋጀ የተናገሩት ሥራ አስፈፃሚው ውይይቱ ሠራተኛው በእኔነት ስሜት እንዲሰራና የተቋሙን ስትራቴጅክ ዕቅድ ውጤታማ በሆነ የአሰራር ስርዓት ለመተግበር ያስችላል።
እንደ አቶ ውድነህ ገለፃ ባለፉት አምስት ዓመታት የዘርፉ የማማከር አቅም እያደገ የመጣ ቢሆንም ከባለድርሻ አካላትና የፕሮጀክት ባለቤቶች ጋር የነበረው ግንኙነት የተጠናከረ አለመሆን፣ በፕሮጀክት ሥራ ላይ የባለቤትነት ክፍተቶች መኖርና በዘርፉ ውስጥ ያሉ የሥራ ክፍሎች እንደ አንድ አማካሪ ድርጅት ተቀናጅተው አለመስራት የታዩ ክፍተቶች ናቸው።
በውይይቱ ላይ ከሥራ ክፍሎች አደረጃጀት፤ ከደመወዝና ጥቅማ ጥቅም፣ ከደረጃ ዕድገትና ዝውውር፤ ለሥራ ከሚያስፈልጉ ሶፍትዌሮች፣ አዳዲስ ቴክኖሎጅዎች፣ የሥራ ላይ ደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች እና ከሌሎች ግብዓቶች ቅርቦት ጋር በተያያዘ ከሠራተኞች ጥያቄዎች ተነስተዋል።
በተጨማሪም ከስልጠና ተደራሽነት፣ ከሥራ መዘርዝርና የሠራተኞችን ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ እየተከናወነ ስላለው ሥራ በተመለከተ ከሠራተኞች ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
በውይይቱ ላይ ተገኝተው ከሠራተኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የሰው ኃይል ሥራ አስፈፃሚ አቶ አታላይ አበበ የሠራተኛውን የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ለመመለስ ከዚህ በፊት ጥናት መደረጉን አስታውሰው
ጥናቱ ላይ ማሻሻያ በማድረግ አሁን ካለው የኑሮ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከደመወዝ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ የሥራ ክፍሎች የሠራተኛ ፍልሰቱ እየጨመረ እንደሆነ እና ፍልሰቱን ለመቀነስ የተቋሙን የፋይናንስ አቅም ባገናዘበ መልኩ መፍትሔ ለመስጠት እየተሰራ ነው።
የደረጃ እድገትና ዝውውሩ በህብረት ስምምነቱ ድንጋጌዎች መሠረት እየተፈፀመ እንደሆነ ያነሱት አቶ አታላይ የሠራተኛውን አቅም ለማሳደግ ከሚሰጠው ስልጠና ባለፈ የዕርስ በዕርስ መማሪያ መድረኮችን ማጠናከር እንደሚገባም አፅንዖት ሠጥተዋል።
በተቋሙ የፋይናንስ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደመረ አሰፋ በበኩላቸው ተቋሙ ከኃይል ሽያጭ በተጨማሪ በኢንጅነሪንግ ዘርፍ ከሚከናወኑ ሥራዎች ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ገልፀው ዘርፉ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በማስፉት ለተቋሙ ስትራቴጅክ ዕቅድ ስኬት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
የሠራተኛውን የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ለመመለስ ተቋሙ ገቢ የሚያገኝበትን መንገድ ማሳደግና ወጪዎችን መቀነስ እንደሚገባም አቶ ደመረ አስገንዝበዋል።
የተቋሙ መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ መኮንን ክፍሌ በበኩላቸው ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ በሠራተኞች የሚነሱ ጥያቄዎች መመለስ እንዳለባቸው አንስተው ለዚህም ማህበሩ ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ጋር በመሆን እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የዘርፉ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ውድነህ የማነ
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት ለዘርፉ ሥራ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ግብዓቶችን ለማሟላት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል። የሠራተኛውን አቅም ለማሳደግ የሚሰጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ስልጠናዎችን በአግባቡ መከታተል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ለተቋሙ ስኬት ዘርፉ የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ ለማከናወን በትኩረት እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ ውድነህ ለዚህም ሁሉም በትብብርና በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቀጣይም ለዘርፉ ስኬታማነት ይህን መሠል የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ከሠራተኛው ሃሳቦችን የመቀበልና በግብዓትነት የመጠቀም እንዲሁም ለጋራ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከየዘርፉ ሥራ አስፈፃሚዎች ጋር በትብብር የመስራቱ ልምድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።





