ተቋማዊ ሥጋቶችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ ያስፈልጋል

ተቋማዊ ሥጋቶችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ ያስፈልጋል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያከናውናቸውን የኃይል መሠረተ ልማቶች ግንባታና የኦፕሬሽን ሥራዎች ሊጎዱ የሚችሉ ስጋቶችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚገባ ተጠቆመ ። የኢፌዲሪ የመንግሥት የልማት ድርጀቶች ይዞታና አስተዳደር የተቋሙን 9 ወራት ክንውን ገምግሟል።

የተቋሙን የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም ሲዓ ተቋሙ በፕሮጀክት ግንባታ፣ በኦፕሬሽን፣ በለውጥ ሥራዎች፣ በፋይናንስ እንዲሁም በሠው ኃይል አስተዳደርና አቅም ግንባታ የነበረውን አፈፃፀም አቅርበዋል።

በግንባታ ላይ ያሉ የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የፊዚካል አፈጻጸም  ከ70 በመቶ በላይ እና የፋይናንስ ደግሞ ከ66 በመቶ በላይ እንደሆነ በሪፖርቱ አመልክተዋል።

እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ በጸጥታ ችግር ግንባታቸው ከተስተጓጎሉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ውጪ ያሉ ፕሮጀክቶች አማካይ አፈጻጸም ከ85 በመቶ በላይ ደርሷል።

ተቋሙ በኦፕሬሽን ዘርፍ ከ15 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል በማምረት የዕቅዱን 94 በመቶ ማሳካቱን የገለፁት አቶ አንዱዓለም ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ14 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ብለዋል።

ተቋሙ ከሃገር ውስጥ የኃይል ሽያጭ   13 ነጥብ 8 ቢሊዮን ለመሠብሰብ አቅዶ 14 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በመሠብሰብ ከዕቅድ በላይ ማሳካት ቢችልም ከኃይል ኤክስፓርት የተገኘው ገቢ ግን ከዕቅዱ ያነሰ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሠው ኃይል አስተዳደር ስምሪትና አቅም ግንባታ፣ በለውጥ ሥራዎች እንዲሁም ሀብትን በማስተዳደር የታዩ አፈጻጸሞች አበረታች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የኢነርጂ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሀገሬ ውሂብ በበኩላቸው የኃይል ምርት ዕድገትና የአቅርቦት መሻሻሎች፣ ተቋሙን ለማዘመን እየተሠሩ ያሉ የለውጥ ሥራዎች፣ ወቅታዊ የሂሳብ መግለጫ ዝግጅት እንዲሁም ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም የማከናወን ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ውዝፍ የውጭ ሀገር የኃይል ሽያጭ ገቢን በመሠብሰብ፣ የታሪፍ ጥናትን አስፀድቆ ተግባራዊ በማድረግ እና የብድር ክፍያ አፈጻጸምን በማሻሻል የተቋሙን የፋይናንስ ቁመና ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል።

ተቋሙ የለያቸውን የፀጥታ ስጋቶች፣ የኃይል መሠረተ ልማት ሥርቆት፣ የካሳ ክፍያና ወሠን ማስከበር እንዲሁም የታሪፍ ተመጣጣኝ አለመሆን እና የውጭ ምንዛሬ ለውጥ ስጋቶችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን  ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በግምገማው ማጠቃለያ ላይ እንደገለፁት የተቋሙን ወጭ የሚቀንሱ አሠራሮችን በመዘርጋት እና የገቢ ማስገኛ አማራጮችን በማስፋት የተቋሙን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ በትኩረት ይሠራል።

ተቋሙ የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝና ተደራሽ በማድረግ ደንበኞቹን ለማርካት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

ዘርፉን የሚጎዱ የሥጋት አካባቢዎችን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጡ አማራጮች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አረጋግጠዋል።

ከፀጥታና ከመሠረተ ልማት ስርቆት ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ከሚመለከታቸው የክልል መስተዳድሮች ጋር በመመካከር ለመፍታት አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል።

Scroll to Top