ጉብኝቱ የኢንደስትሪ ምርቶችን ለማሳወቅ እና የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለመጠቀም ለተቋማት ዕድል የሚፈጥር ነው

ጉብኝቱ የኢንደስትሪ ምርቶችን ለማሳወቅ እና የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለመጠቀም ለተቋማት ዕድል የሚፈጥር ነው

በሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በሀገር ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ የኢንደስትሪ ምርቶችን ለማሳወቅ እና የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለመጠቀም ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ተናግረዋል።

የተቋሙ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ከግንቦት 1 እስከ 5 ቀን 2016 ዓ.ም እየተካሄደ ያለውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት በተቋሙ የኢንጅነሪንግ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ውድነህ የማነ እንደገለፁት ጉብኝቱ ሀገሪቱ እየሄደችበት ያለውን የኢንዱስትሪ ጉዞ ለማወቅና ተቋማት ከሃገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ምን ዓይነት ምርቶችን ማግኘትና መጠቀም እንዳለባቸው ለመለየት ያስችላል።

በሀገር ውስጥ ይመረታሉ ተብለው የማይታሰቡ እና ለተቋሙ ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ ምርቶችን በጉብኝቱ ላይ መመልከታቸውንም አንስተዋል።

መንግስት የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተቋሙ የሀገር የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለመጠቀም ዝግጅት እያደረገ እንደሆነም ሥራ አስፈፃሚው አመላክተዋል።

ተቋሙ ከዚህ በፊት ከኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ጋር ስምምነት በማድረግ ወደ ሥራ መግባቱን ያወሱት አቶ ውድነህ በቀጣይ በኤክስፖው ላይ ከተሳተፉ አምራች ድርጅቶች ጋር ስምምነት በማድረግ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለመጠቀም በቁርጠኝት እየሰራበት እንደሆነም ተናገረዋል። ይህም ለተቋሙ የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት በኩል ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።

በዐውደርዕዩ ላይ የቀረቡ ምርቶች በሀገሪቱ ኢንደስትሪዎች እየተስፋፉ መምጣታቸውን የሚያሳዩ ናቸው ያሉት አቶ ውድነህ ይህም ተቋሙ የኢንደስትሪዎችን ዕድገት ታሳቢ ያደረገ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ በትኩረት መሠራት እንዳለበት ያመላከተ ነው፡፡

በተቋሙ የዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት የአስተዳደራዊ ጉዳዮች እና ዶክመንቴሽን ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ በበኩላቸው ጉብኝቱ ከተቋሙ የሥራ ባህሪ ጋር የሚገናኙ የተለያዩ ምርቶችን በመውሰድ ጥቅም ላይ ለማዋል ዕድል ይፈጥራል።

እንደ ኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ ያሉ ምርቶች በአውደ ርዕዩ ላይ መቅረባቸውን ያነሱት ስራ አስኪያጁ ይህም በሀገር ውስጥ ምርት ሀገራዊ ተቋም ለመገንባት እየተሰራ ካለው ስራ በተጨማሪ ለተሸከርካሪዎቹ ከሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ገቢ ለማግኘት ያስችላል፡፡

በጉብኝቱ ላይ ከተሳተፉት የተቋሙ ሠራተኞች መካከል አቶ ደረሰ ዳንኤል እና አቶ ዳንኤል ተስፋዬ እንደተናገሩት የተቋሙ ሠራተኞች አውደርዕዩን እንዲጎበኙ መደረጉ ሀገሪቱ በኢንደስትሪው ዘርፍ የምታከናውናቸውን ሥራዎች እንዲያውቁ ዕድል ይፈጥራል።

ጉብኝቱ ሠራተኛው የኢንደስትሪ ቴክኖሎጅዎችን እንዲያውቅ ከማድረጉ በተጨማሪ በሀገሪቱ ላይ ያለውን የተዛባ አመለካከት እንደሚቀይር ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ለማስገንዘብ ይህን መሰል ጉብኝት መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ከግንቦት 1 ቀን እስከ 05 ቀን 2016 ዓ.ም በኢንደስትሪ ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የዘንድሮው ለ3ኛ ጊዜ የተዘጋጀ ነው።

Scroll to Top