የማህበረሰባዊ እሴቶችን በመጠቀም የመሠረተ ልማት ስርቆትን መከላከል ተችሏልየኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆትን ለመከላከል ከመደበኛው ህግ በተጨማሪ የማህበረሰቡን እሴት መጠቀም ውጤት እያመጣ መሆኑን በማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ዘርፍ የሰሜን ምስራቅ ሪጅን 2 መምሪያ ገለፀ፡፡
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ሀሰን መሃመድ እንደገለፁት በ2016 በጀት ዓመት 10 ወራት ውስጥ ሪጅኑ በሚያስተዳድራቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ምንም ዓይነት ስርቆት አልተፈፀመም፡፡
በ2015 በጀት ዓመት 2 የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ ስርቆት መፈፀሙን ያስታወሱት አቶ ሀሰን በዳጉ የመረጃ መቀባበያ ስልት ክትትል ተደርጎ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የክልሉ የፀጥታ ቢሮ እና ሪጅኑ በመተባበር ለእያንዳንዱ ወረዳ እንዲሁም የአካባቢው የጎሳ መሪዎች ስለ መሰረተ ልማት ጥበቃ የማስገንዘብ ሥራ ተሰርቷል፡፡
አካባቢው ሙቀት በመሆኑ ኤሌክትሪክ ለማህበረሰቡ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ያነሱት ዳይሬክተሩ ማህበረሰቡም ለመሠረተ ልማቱ የሚሰጡት ትኩረት ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ስርቆት የማህበረሰቡ መልካም እሴት ባለመሆኑ በሪጅኑ ውስጥ የሚስተዋሉ የስርቆትና መሰል ተግባራትን በሚፈጽሙ አካላት ላይ የአፋር ህዝብ እሴት በሆነው የዳጉ መረጃ መቀባበያ ሥርዓት ክትትል ተደርጎ ለህግ እንደሚቀርቡም ነው የተገለፀው፡፡
የሰሜን ምሥራቅ ሪጅን 2 ሦስት የማከፋፈያ ጣቢያና 450 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመሮች አሉት፡፡