በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚገኙ የሴት ሠራተኞች እና የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተቋሙ የሥራ ቦታዎች የሚገኙ የሥርዓተ ፆታ ተወካዮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው በተቋሙ የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች መምሪያ አሳሰበ።
መምሪያው የሥርዓተ ፃታ ጉዳይን በተቋሙ የሥራ ቦታዎች ወጥነት ባለው መልኩ ለመተግበር የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በሪጅኖች፣ ማመንጫ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለሚገኙ የሥርዓተ ፆታ ጉዳይ ተወካዮች መስጠት ጀምሯል።
የመምሪያው ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኤዲኤ እንደተናገሩት በተቋሙ የሥራ ቦታዎች የሥርዓተ ፆታ ጉዳይን ወጥነት ባለው መልኩ በመተግበር ላይ ክፍተቶች ይስተዋላሉ።
ተወካዮቹ በሥርዓተ ፆታ ፅንሰ ሃሳብ እና በአሰራር መመሪያው ላይ የግንዛቤ ክፍተቶች ስላሉባቸው የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮችን ወጥነት ባለው መልኩ መተግበር እንዳልተቻለ ዳይሬክተሯ አንስተዋል።
እንደ ወ/ሮ ሌንሴ ገለፃ ስልጠናው በስርዓተ ፆታ ፅንሰ ሃሳብ ላይ ግንዛቤ በመያዝ የሴቶችን ተጠቃሚነት በእውቀት ላይ ተመስረተው እንዲሰሩ ለማድረግ እና የአሰራር መመሪያውን በአግባቡ ለመተግበር ያግዛል።
የሥርዓተ ፃታ ጉዳይን በተቋሙ የሥራ በታዎች ወጥነት ባለው መልኩ ለመተግበር እና ተወካዮቹ ሥራቸውን በትብብር እንዲሰሩ ለማስቻል ስልጠናው ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም አመላክተዋል።
በተቋሙ የሚከናወኑ ሥራዎች የሥርዓተ ፆታ ጉዳይን ባካተተ መልኩ እንዲፈፀሙ ተወካዮች በሥራ ቦታቸው ባሉ የተለያዩ ኮሚቴዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ያነሱት ዳይሬክተሯ ለዚህም በየሥራ ቦታዎቹ የሚገኙ ኃላፊዎች የሥርዓተ ፆታ ተወካዮችን በኮሚቴ አባልነት ማካተት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ከሥርዓተ ፃታ አካታችነት ጎን ለጎን የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሥራ ቦታዎች ላይ ምቹ የሥራ ከባቢ እንዲፈጠር ተወካዮቹ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል ።
ከግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው በተጨማሪ ተወካዮች እያጋጠሟቸው ባሉ ችግሮች ላይ ውይይት በማድረግ በቀጣይ ድጋፍ የሚደረግበት አሰራር እንደሚዘረጋ ዳይሬክተሯ አረጋግጠዋል።
ተሳታፊዎቹ ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል ወደ ሥራ ቦታቸው ሲመለሱ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ከግንቦት 8 እስከ 9 ቀን 2016 ዓም እየተሰጠ ባለው ስልጠና ላይ 24 የሥርዓተ ፆታ ጉዳይ ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።





