ለኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግብዓት አቅርቦት የፊርማ ስምምነት ተከናወነ                    

ለኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግብዓት አቅርቦት የፊርማ ስምምነት ተከናወነ                    

ሥምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ  ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ናቸው፡፡

ሥምምነቱ በዋናነት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሚገነባቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ግብዓት የሚሆኑ ዕቃዎችን አምርቶ ለማቅረብ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢ/ር አሸብር ባልቻ በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው ሥምምነት ሃገራዊ ምርትን በመጠቀም የውጭ ምንዛሬን ለማዳንና ጊዜን ለመቆጠብ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡

እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ለተቋሙ  የሚያስፈልጉ የኤሌክትሪክ ግብዓቶችን ከሃገር ውስጥ ማሟላት ከተቋሙም አልፎ ለሃገራዊ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡   

የሁለቱን ተቋማት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጠው ይህ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የኢፌዴሪ የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ላደረገው ድጋፍ ሥራ አስፈፃሚው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሥራ አስፈፃሚው አክለውም የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ተቋሙ በቅርቡ ለሚጀምራቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት የሚያገለግሉ ግብዓቶችን ማምረት እንዲጀምር እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ 

የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በበኩላቸው ተቋማቸው የሚያመርታቸውን የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግብዓት ለተቋሙ ትልቅ ጥቅም እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በውጭ ምንዛሬ ማስገባት ተቋማዊ ዕደገትን የሚያቀጨጭ እና የሃገር ኢኮኖሚን የሚጎዳ በመሆኑ የራስን ምርት በጥራት አምርቶ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

የሃገር ውስጥ ምርቶች ጥራት የላቸውም የሚል አመለካከት መኖሩን የጠቀሱት አምባሳደሩ ይህን አመለካካት የሚያስቀይር ሀገሪቱ ጥራት ያላቸው ምርቶችን በማምረት ከራስ ፍጆታ አልፎ ለዓለም አቀፍ ገበያ እያቀረበች መሆኑን  አስረድተዋል።

የራስን ምርት አክብሮ መጠቀም ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ከሌሎች ሃገራት ብዙ ተሞክሮ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሚገነባቸው የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ተቋሙ በሚፈልገው ዓይነትና ጥራት አምርቶ ለማቅረብ ድርጅታቸው ቁርጠኛ ነው።  በሁለቱ ተቋማት መካከል የተፈረመው ሥምምነት ከምርት አቅርቦት በተጨማሪ የሠው ሃይል አቅምን ለማሳደግና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የማኑፌክቸሪንግ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ገረመው ቀኖ  ሁለቱ ተቋማት ያደረጉት ሥምምነት የልማት ድርጅቶች ተባብረው በመሥራት በጋራ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም በመሠረተ ልማት ግንባታ፣በኢንዱስትሪ እና በሌሎች ምርቶች የተሰማሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች በጋራ ሰርተው ለውጥ እንዲያመጡ ዘርፋቸው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ገረመው ተናግረዋል፡፡

Scroll to Top