የገንደ አርባ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ40 ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ እንደሚያቀርብ የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ገቢታ ኢረጎ እንደገለፁት የማከፋፈያ ጣቢያው መጠናቀቅ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኩን ወደ ሙሉ የማምረት አቅም ለማሸጋገርና ለኢንቨስትመንት መፋጠን ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

ፓርኩ ካረፈበት 271 ሄክታር መሬት ውስጥ 136 ሄክታሩ ለኢንዱስትሪዎች ልማት የሚውል መሆኑን ጠቁመው ይህንኑ ግዙፍ የልማት ቀጠና ለማንቀሳቀስ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደሚያስፈልገው ነው ያብራሩት።
በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪ ፓርኩ ምርታቸውን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሰሩ ለሚገኙ ፋብሪካዎች እያቀረበ ያለው የኃይል መጠን ከ5 ነጥብ 8 ሜጋ ዋት እንደማይበልጥ ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ በቂ ባለመሆኑ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ነው የጠቆሙት።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ለማምረት ውል ከተዋዋሉት 40 ባለሃብቶች ውስጥ 10 ባለሀብቶች በፓርኩ ውስጥ የግብርና ውጤቶችን በማቀነባበር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገቢያ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኩ ኃይል የሚያገኘው ከአዳሚ ቱሉ መስመር ላይ በመሆኑ ፋብሪካዎቹ ለተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥና የቮልቴጅ መዋዠቅ ችግሮች እየተጋለጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡


የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ አስተማማኝና ያልተቆራረጠ ኃይል ለማቅረብ ከማገዙም ባሻገር በኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ወደ ሥራ መግባት ያልቻሉ ፋብሪካዎች በቀጥታ ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ይህም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ለግብርና ምርቶች እሴት ለመጨመር እና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግ እንዲሁም አዳዲስ ባለሃብቶችን ወደ ፓርኩ ለመሳብ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል።

