ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው

ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው

በኦሞ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘው የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ከኃይል ማመንጫነት ባለፈ ለዜጎች ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን የአካባቢው መስተዳድር አካላት እና የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች ገለፁ፡፡

ከመሎኮዛ ወረዳ፣ ከጎፋ ዞን እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስትና ከምክር ቤት የተውጣጡ አመራሮች ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በፕሮጀክቱ በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የመሎ ኮዛ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉነህ አውሳቶ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ለሀገር ብርሃን ከመሆን ባለፈ ለመሎ ኮዛ ሕዝብ አዲስ ተስፋን የፈነጠቀ ነው።

በፕሮጀክቱ ምክንያት የተገነቡት መሰረተ ልማቶች አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን በቀላሉ ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ ከማስቻላቸውም በላይ ለረጅም ዘመናት በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ተለያይተው የነበሩትን የጎፋና የኮንታ ዞን ህዝቦችን ማገናኘት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳ ፕሮጀክቱ ትልቅ ተስፋ ይዞ የመጣ ቢሆንም በግንባታው አቅራቢያ የሚገኙ ቀበሌዎች አሁንም በጨለማ ውስጥ በመሆናቸው በአፋጣኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስተዳዳሪው ጥያቄ አቅርበዋል።

የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ምናሴ ኤሊያስ በበኩላቸው አካባቢው ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖረውም በመንገድ እጥረት ምክንያት በስፋት ለማምረትና ለገበያ ለማቅረብ አዳጋች ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በመሆኑም ፕሮጀክቱ መምጣቱ ለዘመናት ተዘግቶ የነበረውን የልማት በር የከፈተ የዕድለኝነት መገለጫና ከፈጣሪ የተሰጠ ታላቅ ስጦታ መሆኑን በመጥቀስ ለመንግስትና ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ መንግስቱ ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ሲሰጡ ተቋሙ በኃይል ማመንጫዎች አካባቢ ለማህበረሰቡ ልማት የማከናወን ልምድ ቢኖረውም የኮይሻ ፕሮጀክት ግን በዓይነትም ሆነ በስፋት ልዩ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይም በኦሞ ወንዝ ላይ የተገነባው ታላቁ ድልድይ በመሻገሪያ እጥረት ተለያይተው የነበሩ ማህበረሰቦችን በማገናኘት ረገድ ተቋሙ የታሪክ አሻራ ያሳረፈበት ፈር ቀዳጅ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢውን ቀበሌዎች የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግም የተጀመረው ሥራ በቅርብ ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አረጋግጠዋል።

የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው አካባቢው የኢነርጂ እና የቱሪዝም ዘርፎችን በማስተሳሰር ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህም እንደ ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ እና የሃላለ ኬላ ሎጅ ካሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ጋር ተዳምሮ ፕሮጀክቱ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ለሕዝቦች ትስስር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል።

ተቋሙ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲኖር የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ በስኬት እንዲወጣ የሚመለከታቸው የመስተዳድር አካላት እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶችን ለመከላከል ጥብቅ ቁጥጥርና ጥበቃ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የፕሮጀክቱ የአካባቢና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው ደሳለኝ የፕሮጀክቱ አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎች አስቀድመው በጥናት መለየታቸውን ጠቁመው ተቋሙ የሥራ ተቋራጩን በማስተባበር መንገድ፣ ድልድይ፣ ትምህርት ቤቶችንና ጤና ጣቢያዎችን በመገንባት ለሕዝብ ማስረከቡ የማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።

በጥናት ላይ ተመስርተው የተከናወኑ የማህበራዊ ልማት ስራዎች በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠርና የአኗኗር ዘይቤያቸው እንዲሻሻል በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

Scroll to Top