በፕሮጀክት የሚከናወኑ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጽዖ እያበረከቱ ነው

በፕሮጀክት የሚከናወኑ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጽዖ እያበረከቱ ነው

የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን ያከናወናቸው የማህበራዊ ኃላፊነት ተግባራት የህብረተሰቡን አኗኗር ዘይቤ ማሻሻላቸውን የፕሮጀክቱ የአካባቢና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው ደሳለኝ እንደገለጹት ተቋሙ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከሠራቸው ሥራዎች መካከል በፕሮጀክቱ ዙሪያ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ120 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የጠጠር መንገድ ግንባታ በዋነኝነት ይጠቀሳል።

በፕሮጀክቱ አቅራቢያ ከተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ባሻገር  በኦሞ ወንዝ ላይ የተገነባው 175 ሜትር ርዝማኔ ያለው ድልድይ ቀደም ሲል በአካባቢው የነበረውን ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር የቀረፉና የጎፋ እና ኮንታ ዞኖች ህዝቦችን ማገናኘታቸውን ገልፀዋል።

እንደ አቶ ግዛቸው ገለፃ ከግንባታው በፊት በሁለቱ ዞኖች መካከል የሚኖሩ ህዝቦች ወንዙን ለመሻገር በዋናተኞች የታገዘ አደገኛ ጉዞ ለማድረግ ይገደዱ ነበረ፡፡

በዚህም ምክንያት በውሃ የመወሰድ እንዲሁም በአዞ የመበላት አደጋ ይከሰት እንደነበር አስታውሰዋል።

ወንዙን የተሻገሩ ሰዎች በሠላም ከውሃው መውጣታቸውን ለማሳወቅ ጭስ በማጨስ ወይም እንጨት በማንደድ ምልክት ይሰጡ የነበረበት ዘመን አሁን ላይ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር ፕሮጀክቱ የገነባቸው መሠረተ ልማቶች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገራቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ነዋሪዎች ያመረቷቸውን የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የቡና እና የማር ምርቶች በቀላሉ ወደ ገበያ ማቅረብ መቻላቸውን የተከናወነው የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራ ያመጣው ውጤት ነው ብለዋል።

ይህም ቀደም ሲል በገበያ እጥረትና በትራንስፖርት ችግር ይባክን የነበረውን የአርሶ አደሩን ድካም ወደ ተጨባጭ ገቢ በመለወጥ ማህበረሰቡ በሀገሪቱ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ዕድል ፈጥሮለታል።

የተከናወኑት የማህበረሰብ ልማት ሥራዎች ፕሮጀክቱ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቅቡልነት እንዲኖረው ከማድረጋቸውም በላይ ህዝቡ ለፕሮጀክቱ ጥበቃና ደህንነት የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ማድረጋቸውን አቶ ግዛቸው ገልጸዋል።

ይህም ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት በመስራት የህብረተሰቡብ አኗኗር የሚቀይር ሥራ ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው የሚያሳይ ተግባር ነው ብለዋል።

Scroll to Top