በተቋሙ የተዘረጋው የመሠረተ ልማት ደህንነት አስተዳደር አሰራር ውጤት እያስገኘ ነው

በተቋሙ የተዘረጋው የመሠረተ ልማት ደህንነት አስተዳደር አሰራር ውጤት እያስገኘ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አዲስ የተዘረጋው የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ደህንነት አስተዳደር አሰራር ውጤት እያስገኘ መሆኑን በዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት የተቋማዊ የመስረተ ልማት ደህንነት አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ፍራፊስ በቀለ እንደገለጹት ተቋሙ በመሠረተ ልማቶቹ ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶችን ለመከላከል የተቋማዊ የመስረተ ልማት ደህንነት አስተዳደር ቢሮ በመክፈት ወደ ሥራ ገብቷል።

ቢሮው በ13ቱም የተቋሙ ሪጅኖች ከመከላከያ የተውጣጡ ከፍተኛ መኮንኖችን በመመደብ የጥበቃ ሥራውን በቅርበት እንዲመራና ከፌዴራልና ከክልል የፀጥታ አካላት እንዲሁም በየደረጃው ከሚገኙ የመስተዳድር አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር እንዲኖር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የግንኙነት ዘዴዎችን በመጠቀምና ከማዕከል እስከ ሪጅን ድረስ የ24 ሰዓት የክትትልና የሪፖርት መለዋወጫ ሥርዓት በመዘርጋት የጥበቃና ቁጥጥር ሥራው በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል።

በተለያዩ አካባቢዎች ከህብረተሰቡ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ህዝቡ በመሰረተ ልማቶችን ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው መደረጉንና ጥቆማዎችን በመስጠት ረገድ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ በመቻሉ የተሰረቁ ንብረቶች ለተቋሙ እንዲመለሱ መደረጉን አብራርተዋል።

ቀደም ሲል በፍትህ አካላትና በፀጥታ መዋቅሮች ዘንድ በመሠረተ ልማት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በቀላል መንገድ የማየትና ተጠርጣሪዎችን በዋስ የመልቀቅ ችግሮች እየተስተካከሉ መምጣታቸውን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚኖረውን ሚና ተገንዝቦ የሀገር ሀብት የሆነውን የኃይል መሠረተ ልማት ከውድመት የመጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሥራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል።

Scroll to Top