በተቋሙ የሚወጡ ፖሊሲዎች ጥራት ያላቸውና የተናበቡ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው

በተቋሙ የሚወጡ ፖሊሲዎች ጥራት ያላቸውና የተናበቡ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው

‎በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚወጡ ፖሊሲዎች ጥራት ያላቸው፣ አሰራርን የሚያቀላጥፉ እና የተናበቡ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በተቋሙ የፖሊሲ፣ ፕሮሰስና የለውጥ ሥራ አመራር መምሪያ ገለጸ።

‎መምሪያው ከተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ የሙያ ደህንነት እና ጤንነት ቢሮ ጋር በሥራ ላይ ጤናና ደህንነት ረቂቅ ፖሊሲ ዙሪያ ከሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት ተካሂዷል።

‎የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም ኪዳኔ እንደገለጹት ተቋሙ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያለውን አቋምና አቅጣጫ የሚያመላክቱ እንዲሁም አሰራርን ውጤታማ የሚያደርጉ የተለያዩ ፖሊሲዎች በዝግጅት ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡

በዛሬው ዕለት የተካሄደው ውይይት በሥራ ላይ ጤናና ደህንነት ረቂቅ ፖሊሲ ዙሪያ በተቋሙ ውስጥ ካሉ የሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች ጋር በመወያየት ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሰል ውይይቶች የሚሰበሰቡ ግብዓቶች ፖሊሲዎች ከመጽደቃቸው በፊት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ኃሳቦች ያካተቱ፣ የተናበቡና የዳበሩ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡

‎ረቂቅ ፖሊሲውን ያቀረቡት የሥራ ላይ ደህንነትና ጤና ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኮርሳ ተሬሳ በበኩላቸው በተቋሙ የሥራ ላይ ደህንነትንና ጤንነት ጉዳይን ሁሉም በባለቤትነት እና በኃላፊነት ስሜት ወስዶ እየሰራ ባለመሆኑ የተለያዩ አደጋዎች እንደሚያጋጥሙ አንስተዋል፡፡

ከሥራ ላይ ጤናና ደህንነት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍና ቀጣይነት ያለው መሻሻል ለማስመዝገብ ፖሊሲው የISO 45001 እና ሌሎች የሀገሪቱን ሕጎች ከግምት ባስገባ መልኩ መዘጀቱን ተናግረዋል።

የሥራ ላይ ደህንነትንና ጤንነት በሰውና በንብረት እንዲሁም በተቋም ገጽታ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን ከግምት በማስገባት ሁሉም የተቋሙ ሥራዎች ከፖሊሲው ጋር ተናበው እንዲሰሩ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‌‎በውይይቱ የተነሱና ሊካተቱ የሚገባቸው ሀሳቦችን በቀጣይ በፖ‎ሊሲው ላይ በማካተት በዘርፉ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራም አብራርተዋል፡፡

‎ተወያዮቹም በፖሊሲው ላይ ሊስተካከሉ፣ ሊካተቱና ሊብራሩ ይገባሉ ያሏቸውን ሀሳቦችና አስተያየቶች አንስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

Scroll to Top