በአርባምንጭ ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እና የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በከተማዋ ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያነቃቃው የከተማዋ ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደስታ ደንበላ እንዳስታወቁት ከተማዋ የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል በመሆኗ በግንባታ ላይ የሚገኘው የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሲጠናቀቅ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
በከተማዋ የቱሪዝም መዳረሻ ይሆናል ተብሎ በመገንባት ላይ ለሚገኘው የ’ገበታ ለትውልድ’ ፕሮጀክት እንዲሁም ሌሎች መንግስታዊ እና የግል የቱሪዝም መዳረሻዎች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ቁልፍ መሰረተ ልማት መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል።


የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ያሉት አቶ ደስታ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በአካባቢው ያለውን የቱሪዝም ፍስት አሁን ካለው በበለጠ ሁኔታ ያነቃቀዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ቱሪስቶች የከተማዋን መስህቦች የሚጎበኙት በቀን ብቻ ስለነበር የኃይል አቅርቦቱ አስተማማኝነት ማደግ ቱሪስቶች በማታም ጭምር መጎብኘት የሚችሉበትን ሰፊ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
እንደ አቶ ደስታ ገለፃ የኃይል አቅርቦቱ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አገልግሎታቸውን በአግባቡ እንዲያቀርቡ በማድረግ የቱሪስቶችን እርካታ ለማሳደግ ያስችላል። ይህም የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ከተማዋ ብሎም ሀገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ያግዛል ነው ያሉት ኃላፊው።


