የባለሙያዎችን የዲጂታል ክህሎት ለማሳደግ የሚያስችል ሥልጠና እየተሰጠ ነው

የባለሙያዎችን የዲጂታል ክህሎት ለማሳደግ የሚያስችል ሥልጠና እየተሰጠ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከማዕከላዊ ሪጅን 1፣ 2 እና 3 እንዲሁም ከረጲ የደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለተውጣጡ ባለሙያዎች የዲጂታል ክህሎት ማሳደጊያ ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።

የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ተወካይ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ጽዮን በቀለ እንደገለጹት ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት በዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ላይ በርካታ ተግባራትን ለማከናወን አቅዶ እየሰራ ነው፡፡

እስከአሁን ወደ ሥራ የገቡትንና በቀጣይም የሚተገበሩትን ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶች በአግባቡ ለመጠቀምና ውጤት ለማስመዝገብ በዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ዙሪያ በቂ ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ሥልጠናው የተቋሙ ሠራተኞችን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ክህሎታቸውን በማዳበር ዝግጁ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ አዳዲስ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ዕቅድ ይዞ እየሰራ ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚዋ ሥልጠናው በቀጣይ ዙሮችም ለሌሎች ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

የፕሮሰስ፣ ፖሊሲና የለውጥ ሥራ አመራር መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አንዷለም ኪዳኔ በበኩላቸው ተቋሙ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከለያቸው አምስት የለውጥ አጀንዳዎች አንዱ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የተቋሙ ሥራዎች ወደ ዲጅታል እየተለወጡ በመሆናቸውና በቀጣይም የአሰራር ሥርዓቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁት ዳይሬክተሩ ሠራተኞች እና የሥራ መሪዎች የዲጂታል መሣሪያዎችን መጠቀም የሚያስችል ዕውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

እንደ ሀገር የዲጅታል 2030 ስትራቴጂ ይፋ ሆኖ ወደ ተግባር ከተገባ በኋላ ተቋሙ ከሀገራዊ ዕቅዱ ጋር የተስማማና ሥራዎቹም ዘመኑን የዋጁ እንዲሆኑ ለማድረግ መሰል የዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት ሥልጠናዎች አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሥልጠናው ለቀጣዮቹ አስር ቀናት የሚቀጥል ይሆናል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top