የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለወላይታ ሶዶ ኮንቨርተር ጣቢያ ግንባታ የግጦሽ መሬታቸውን በካሳ ለለቀቁ ነዋሪዎች መልሶ ማቋቋሚያ የገነባው የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በአካባቢው ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ እንዲስፋፋ እንደሚያግዝ ተገለፀ።
የወላይታ ሶዶ ኮንቨርተር ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ግርማ እንደገለፁት ጣቢያው ከተሰጠው ሀገራዊ ተልዕኮ በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎችን አከናውኗል።
ተቋሙ ጣቢያው ሲገነባ የግጦሽ ቦታ ለተወሰደባቸው 54 የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች ከካሳ ክፍያ በተጨማሪ በዘላቂነት ሊቋቋሙ የሚችሉበትን የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ ገንብቶ ማስረከቡን አስታውሰዋል።
ተቋሙ ፋብሪካውን ከመገንባት ባለፈ የምርት ሥራውን በአግባቡ ለማከናወን የሚያስችሉ ስልጠናዎችንና የተለያዩ ሙያዊ ድጋፎችን ያደረገ ሲሆን ለሥራ ማስጀመሪያ የሚሆን 60 ኩንታል ጥሬ ዕቃ ማቅረቡንም አቶ ሀብታሙ አብራርተዋል።
የሶዶ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እስጢፋኖስ ዋቴ በበኩላቸው የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካው ለጣቢያው ግንባታ የእንስሳት የግጦሽ መሬት የተወሰደባቸው አርሶ አደሮች የእንስሳት መኖ እንዲያመርቱበትና በዘላቂነት እንዲቋቋሙበት ታሳቢ ተደርጎ መገንባቱን ገልፀዋል።

ፋብሪካው የአካባቢው ማህበረሰብ ልቅ ከሆነ ግጦሽ ወጥቶ እንስሳትን በዘመናዊ መንገድ እንዲያረባ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ሲሆን ይህም የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው እንስሳትን በማርባት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያግዛል ነው ያሉት።
ሰማኒያ የልማት ተነሽ አርሶ አደሮችንና ቤተሰቦቻቸውን ያካተተው የዋጃ ቄሮ ሶፒላ እድገት በኅብረት የእንስሳት እርባታና መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ማህበር ፀሐፊ አቶ አፈወርቅ ኃይለማሪያም እንደገለፁት ፋብሪካው በሰዓት ለከብት 12 ኩንታል እንዲሁም ለዶሮ 18 ኩንታል መኖ የማምረት አቅም አለው፡፡
ይሁንና ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደማምረት ሥራ ሲገባ ከማህበሩ አባላት በተጨማሪ የአካባቢውን ማህበረሰብ በተለያዩ መንገዶች ተጠቃሚ እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል።
የማህበሩ አባል ወ/ሮ የምስራች ካቤ በበኩላቸው በተቋሙ የተገነባላቸው ፋብሪካ ልጆቻቸውን ለማሳደግ እና ሙሉ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር የኢኮኖሚ ዋስትና እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።
“ፋብሪካው ለእኛ ለዛሬ የኑሮ መደጎሚያ ብቻ ሳይሆን ነገ ለልጆቻችን ቅርስም ውርስም ነው” ሲሉም ገልፀውታል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”






