በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሥጋቶችን ቀድሞ በመለየት ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ በተቋሙ የኢትዮ ፓወር አካዳሚ የአመራር ልማት ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ተናኘ መኮንን አስታወቁ፡፡
ሥራ አስኪያጇ በተቋሙ ከተለያዩ ዘርፎች ለተውጣጡ የሥራ መሪዎች በስጋት አስተዳደር ዙሪያ የተዘጋጀውን ስልጠና ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት በግንባታ እና ኦፕሬሽን ላይ ባሉ የማመንጫ፣ ማከፋፈያ ጣቢያዎችና የማስተላለፊያ መስመሮች እንዲሁም በተቋሙ ሁሉም ዘርፎች ስጋቶችን በጥንቃቄ በመለየት ችግር ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ ምላሽ መስጠት ይገባል፡፡


የተቋሙ የሥራ ባህሪ ከስጋት ጋር የተገናኘ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ተናኘ የሚሰጠው ስልጠና ስጋቶችን በመቀነስ እንደተቋም ሊደርስ የሚችል አደጋን ለመከላከል ያስችላል ብለዋል፡፡
በተለያዩ ዘርፎች የሚሰጡ ሥልጠናዎች የተቋሙን ስትራቴጅካዊ ግቦች በማሳካት በኩል ለውጥ እንዲያመጡ በተለይ የሥራ ኃላፊዎች ሥልጠናዎችን ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው ሥራ አስኪያጇ አሳስበዋል፡፡
በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ የተቋም ስጋት አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ህሊና አለማየሁ በበኩላቸው በተቋሙ ውጤታማ የሥጋት አስተዳደር ሥርዓትን በመዘርጋት የሚያጋጥሙ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት ስልጠናው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አካታች የስጋት አስተዳደር ዕቅዶች እና መርሆች፣ ሂደቶች እና የስጋት አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያጋጥሙ ችግሮችና መወሰድ ያለባቸው የመፍትሔ አማራጮች ስልጠናው ትኩረት ከሚያደርግባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የፋይናንስና የቴክኖሎጅ እጥረቶች እንዲሁም የሥጋት አስተዳደርን እንደ ተጨማሪ ሥራ ማየት በተቋሙ የሥጋት አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅፋት መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ እንደተቋም የተለዩ ስጋቶች መለየታቸውን የተናገሩት ሥራ አስኪያጇ የሥራ ኃላፊዎች የሥጋት አስተዳደር ዕቅድ በማዘጋጀት ከሥራዎቻቸው ጋር አስተሳስሮ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በተቋሙ የሚለዩ ሥጋቶች ተቋሙ ያለበትን ኃላፊነት እና የሚያንቀሳቅሰውን መሰረተ ልማት ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




