ሴቶች ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ ለማስቻል የማብቃትና የመደገፍ ሥራ ሊሰራ ይገባል

ሴቶች ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ ለማስቻል የማብቃትና የመደገፍ ሥራ ሊሰራ ይገባል

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን (ማርች 8) “50ኛ ዓመት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ አንድ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ተከብሯል።

በዓሉ የሴቶችን መብት ለማስከበር፣ የእኩልነት ድምፅን ለማጎልበት እና ሴቶች ለሀገር ብልጽግና የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት ያለመ ነው።

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች 3 ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ጥሩ ወርቅ ሽፈራው ሴቶች ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ ለማድረግ ማብቃትና መደገፍ ያስፈልጋል።

ሴቶች በዓሉን ከማክበር ባለፈ በእያንዳንዱ የሥራ መስክ ላይ ውጤታማ እና አርዓያ ሆነው መገኘት እንዳለባቸውም ነው የገለፁት።

እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ሴቶች በሁሉም ዘርፍ የሚታገዙና የሚደገፉ ብቻም ሳይሆኑ ኃላፊነትን መሸከም የሚችሉ ጠንካራና ተወዳዳሪ  ሠራተኞች ለመሆን የትምህርት ደረጃቸውን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል።

የአዳማ አንድ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ አይናለም ወ/ሚካኤል በበኩላቸው በዓሉን ከተለያዩ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከተውጣጡ ሴት ሠራተኞች ጋር በጋራ በማክበራቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

በጀነሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ የፋይናንስና ግዥ መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ እታለም እሸቱ በበኩላቸው ሴቶች ራሳቸውን በትምህርት ማብቃትና ማሳደግ ከቻሉ በሁሉም የሥራ ኃላፊነቶች ላይ አቅማቸውን ማሳየት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ሴቶች የይቻላል መንፈስን በመያዝ በተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

በኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የዲጂታል ሚዲያ እና ፐብሊኬሽን ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሃይኖማኖት ገበየሁ እንደገለፁት ሴቶች በተደራራቢ የሥራ ጫናዎች እና ማህበራዊ ተፅዕኖዎች ሳይገቱ ለዓላማቸው ጠንክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል።

በዕለቱ የበዓሉ ተሳታፊዎች የአዳማ አንድ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖችን የጎበኙ ሲሆን በተቋሙ ለረጅም ጊዜ በቅንነት እና በታማኝነት ላገለገሉ ሴት ሠራተኞችም ዕውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ እና በሀገራችን ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሀግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

Scroll to Top