“የሥርዓተ ጾታ እኩልነት መከበር የሀገራችን ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ አቅም ይፈጥራል” –  አቶ ሙላት ገዛኽኝ

“የሥርዓተ ጾታ እኩልነት መከበር የሀገራችን ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ አቅም ይፈጥራል” –  አቶ ሙላት ገዛኽኝ

የሥርዓተ ጾታ እኩልነት መከበር ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዕድገትና ብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን (ማርች 8) “50 ዓመት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ!” በሚል መሪ ቃል በተቋሙ ተከብሯል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኽኝ በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሲከበር በኢትዮጵያ ብሎም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሴቶች ለመብቶቻቸው በፅናት ታግለው ያስመዘገቧቸው ስኬቶች አብረው ይታሰባሉ፡፡

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ያለሴቶች ተሳትፎ ማሳካት እንደማይቻል የጠቀሱት ኃላፊው ሁሉም ማህበረሰብ ለሴቶች መብት መከበር ተገቢ የሆነ ድጋፍና ትብብር ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

በዓሉ በሃገራችን በሁሉም ዘርፍ ዋጋ ከፍለው ሀገር ያጸኑ ሴቶችን  የምናወድስበት ቀን  ከመሆኑም ባሻገር ለሴቶች እኩልነትና ክብር የሚደረጉ ቀጣይ ትግሎችን አጠናክሮ ለመቀጠል ቃል የምንገባበትም ነው ብለዋል፡፡

የሴቶችን እኩልነት በማረጋገጥ በኩል ለውጦች ቢኖሩም ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ማስቀረት የሁሉም የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በተቋሙ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች  መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ በበኩላቸው የሴቶችን መብትና ጥቅሞች በማስከበር በኩል እንደ ማህበረሰብ ያልተሻገርናቸውን ችግሮች ለመቀየር ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

በተቋሙ ለሚሰሩ ሴቶች ምቹ የሥራ አካባቢ በመፍጠር፣ የትምህር ዕድሎችን በማመቻቸት እና ሴቶችን በአመራር ሰጭነት ቦታዎች በማሳተፍ እየተሰጡ ያሉ ዕድሎችን ተጠቅመው አቅማቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ባለፉት ጊዚያቶች በተቋሙ የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን በመገንዘብ ማኔጅመንቱ በወሰደው እርምጃ ለሴቶች ልዩ ዕገዛዎችን በማድረግ ወደ ተቋሙ እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ያስታወሱት ዳይሬክተሯ የተቋሙ ማኔጅመንት ለሰጠው ፈጣን ምላሽ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Scroll to Top