ሴቶች የኢነርጂ ሽግግር ተቀባዮች ብቻ ሳይሆኑ መሪዎች፣ መሐንዲሶች፣ ፈጣሪዎች እና ውሳኔ ሰጪዎች መሆናቸውን በኢትዮጵያ የሴቶች ኢነርጂ ማህበር አምባሳደር (Ethiopian Women in Energy – EWiEn) ኢንጂነር የምስራች ወርቁ ገለጹ፡፡
ኢንጂነሯ ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን (ማርች 8) ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ሴቶች የኢትዮጵያን ኢነርጂ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመቅረጽ ረገድ የሚጫወቱት ሚና የላቀ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ የሀገራችን የለውጥ ማዕከልና የማዕዘን ድንጋይ በመሆኑ በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ሴቶችን ማሳተፍ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ ያግዛል ብለዋል፡፡



እንደ ኢንጂነሯ ገለጻ ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው ግንባር ቀደም ስኬቶች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደሯ የኢትዮጵያውያን ፅናት እና አንድነት በታየበት በዚህ አስደናቂ ፕሮጀክት ሴቶች ከመሐንዲስነት ጀምሮ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በንፋስ፣ በከርሰ ምድር እንፋሎት እና በሶላር ኢነርጂ ላይ የሚደረጉ የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንቶችን በማጠናከር የኃይል ስብጥሮችን ለማስፋት እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በምታደርጋቸው ጥረቶች ማህበራቸው በኢነርጂ ዘርፉ ላይ የሚሰሩ ሴቶችን ለማገዝና ለማብቃት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሴቶች በቤት ውስጥ እና በሥራ ቦታዎች ለሚገጥሟቸው ውስብስብ ችግሮች ሳይንበረከኩ አቅማቸውን ማሳየት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ጨምሮ በዘርፉ የሚሰሩ ተቋማት እና ፖሊሲ አውጪዎች ሴቶች በኢነርጂ ዘርፍ ያላቸውን አመራር እና እውቀት በመገንዘብ በሴቶች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡




