የሐዋሳ ቁጥር 1 ማከፋፈያ ጣቢያ የከተማዋን 90 በመቶ የኃይል አቅርቦት እየሸፈነ ነው

የሐዋሳ ቁጥር 1 ማከፋፈያ ጣቢያ የከተማዋን 90 በመቶ የኃይል አቅርቦት እየሸፈነ ነው

የሐዋሳ ቁጥር 1 ባለ 132  ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ 90 በመቶ የሚሆነውን የከተማዋን የኃይል አቅርቦት እየሸፈነ መሆኑን የጣቢያው ኃላፊ አቶ ታከለ ተፈሪ ተናገሩ።

አቶ ታከለ እንደተናገሩት ማከፋፈያ ጣቢያው አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ የሐዋሳ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ አገልግሎት መስጠት እስከጀመረበት 2011 ዓ.ም ድረስ ለሐዋሳ ከተማና በዙሪያው ለሚገኙ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያቀርብ ቆይቷል።

ይሁንና የቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ደንበኞችን በማዛወር ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ የተወሰኑ የከተማዋ ደንበኞች ከቁጥር ሁለት ኃይል እንዲያገኙ የተደረገ በመሆኑ በጣቢያው ላይ የነበረውን ጫና በማቃለል በኩል ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

ጣቢያው አሁን ላይ የከተማዋን 90 በመቶ የኃይል አቅርቦት ከመሸፈኑ በተጨማሪ  ወንዶ ገነት፣ ቦሪቾ፣ ይርባ፣ አርቤጎና እና ሌሎች በዙሪያው ለሚገኙ አካባቢዎች ኃይል በማቅረብ በተለያየ መልኩ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ጣቢያው የሐዋሳ ከተማን ጨምሮ በአካባቢው ለሚገኙ ከተሞች መስፋፋት፣  ለኢንቨስትመንት ማደግ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ በአጠቃላይ ለአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መነቃቃት መሠረት የጣለ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል።

ማከፋፈያ ጣቢያው ላለፉት 38 ዓመታት የአካባቢውን የኃይል ጥያቄ በመመለስ ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የመጫን አቅሙ 99 በመቶ በመድረሱ ተጨማሪ ደንበኞችን ማስተናገድ እንደማይችል ገልፀዋል።

ሰለሆነም የኃይል ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ የአቅም ማሳደግን ጨምሮ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ የመቆጣጠሪያ ብሬከሮችን (swcach gear) እና የሲዊች ያርድ የተለያዩ ዕቃዎችን ዘመኑ ወደደረሰበት ቴክኖሎጅ መቀየር እንደሚያስፈልግ አቶ ታከለ ጠቁመዋል፡፡

የሐዋሳ ቁጥር አንድ ማከፋፈያ ጣቢያ 66 ሜጋ ቮልት አምፒር የመሸከም አቅም ያላቸው ሦስት ትራንስፎርመሮች ሲኖሩት ከሐዋሳ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ አንድ ገቢ፣ ስምንት ባለ 15 ወጪ መስመሮች እና ሦስት ባለ 33 ወጪ መስመሮች አሉት።

Scroll to Top