የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል ከሆነው የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 -አርባ ምንጭ ቁጥር 2- አርባ ምንጭ ቁጥር 1 የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ ሥራ የእውቀትና የቴክኖሎጅ ሽግግር ማግኘታቸውን በፕሮጀክቱ ሥራ ላይ የተሳተፉ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተናገሩ።
በደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ ተቋራጭ የምዕራፍ አንድ የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ከበደ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከሚኖረው ሀገራዊና አካባቢያዊ ፍይዳ ባሻገር በግንባታ ሂደት ላይ እያለ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም የእውቀትና ቴክኖሎጅ ሽግግር እንድኖር በማድረግ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የፕሮጀክቱ የእያንዳንዱ ዕቃ ተከላ፣ የጋዝ ሙሌት እንዲሁም የፍተሻና ሙከራ ሥራዎች ሲከናወኑ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ከሥራ ተቋራጭ እና አማካሪ ባለሙያዎች ጋር አብረው እንዲሳተፋ በማድረግ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲቀስሙ ተደርጓል ብለዋል።



በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፕሮጀክቱ የምዕራፍ አንድ ሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ሚጀና በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ሀገር ባለሙያዎች የእርስ በእርስ የዕውቀትና የቴክኖሎች ልውውጥ እንዲያደርጉ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የኤሌክትሪካል መሀንዲስ የሆኑት ፍራኦል ዳዲ እንደተናገሩት ማከፋፈያ ጣቢያው ከቤት ውጪ የጂ.አይ. ኤስ ቴክኖሎጂ (outdoor GIS) የተገነባ ነው።
በጣቢያው የእያንዳንዱ ዕቃዎች የሙከራና ፍተሻ ሥራዎች ላይ ከውጭ ሀገር ዜጎች ጋር በቅንጅት በመስራታቸው ስለ ቴክኖሎጅው ፣ የሙከራና ፍተሻ ሥራዎች የአሰራር ሂደቶች እንዲሁም ሥራውን ለማከናወን ጥቅም ላይ ስለሚውሉ መሳሪያዎች በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
በአርባ ምንጭ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ የሳይት ፎርማን የሆነው ወጣት አስፋው አወና ፕሮጀክቱን ከመቀላቀሉ በፊት በኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ምንም ዓይነት ሙያና የሥራ ልምድ እንዳልነበረው ገልጿል።
ፕሮጀክቱ የሥራ ዕድሉን ከመፈጠሩ በተጨማሪ ከውጭ ሀገር ዜጎች ጋር በመስራቱ በዘርፉ ለቀጣይ ሥራዎች የሚያግዝ ልምድ፣ የእውቀትና የቴክኖሎጅ ሽግግር ማግኘቱን ተናግሯል።
ሌላው በፕሮጀክቱ የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ወጣት ሳይለ ጋሻ ከውጭ ሀገራት ዜጎች ጋር በመስራቱ ቋንቋቸውን ከመልመድ ጀምሮ በኤሌክትሪክ ዝርጋታ እና ግንባታ ሥራዎች ላይ ሙያ መቅሰሙን ገልጿል።
የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 -አርባ ምንጭ 2- አርባ ምንጭ ቁጥር 1 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት በአማካይ 2000 ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩ ተገልጿል።




