የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በአርባ ምንጭ ቁጥር 1 ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ለሚስተዋሉ የኃይል አቅርቦት ችግሮች መፍትሔ እንደሚሰጥ የጣቢያው ኃላፊ ተናገሩ።
ኃላፊው አቶ ምንተስኖት ማሞ እንደተናገሩት የማከፋፈያ ጣቢያው ትራንስፎርመሮች ኃይል የማቅረብ አቅም ቢኖራቸውም ጣቢያው በአንድ አቅጣጫ ብቻ ኃይል የሚያገኝ በመሆኑ፣ ገቢ መስመሩ የፕሮቴክሽን ሥርዓት የሌለው እና በአካባቢው ብቸኛ የኃይል አቅራቢ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአቅርቦቱ ላይ ችግሮች ይስተዋሉ ነበር።

ጣቢያው ለሚያጋጥሙት ችግሮች ከወላይታ ሶዶ ቁጥር 1 ማከፋፈያ ጣቢያ መረጃ በመቀበል እልባት ሲሰጥ እንደነበር እና ይህም ለችግሮቹ በወቅቱ መፍትሔ ለመስጠት በሚከናወነው ሥራ ላይ እንቅፋት ሲፈጥር መቆየቱን ተናግረዋል።
ማከፋፈያ ጣቢያው ለጋሞ ዞን ብቸኛ የኃይል አቅራቢ መሆኑን የገለፁት አቶ ምንተስኖት ከጣቢያው ረጅም ርቀት የተጓዙ እና ተደርበው የወጡ የማሰራጫ መስመሮች በብሬከሮች ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠሩ እንደሆነም አስረድተዋል።
ይሁንና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በጣቢያው ላይ የሚተስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።



ፕሮጀክቱ ነባሩን የአርባ ምንጭ ማከፋፈያ ጣቢያ በመጠናቀቅ ላይ ከሚገኘው የአርባ ምንጭ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ ጋር በቀለበት ስርዓት እንዲያያዝ በማድረግ ጣቢያው በሁለት አቅጣጫ ኃይል የሚቀበልበትን ዕድል እንደፈጠረ አብራርተዋል።
የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የአርባ ምንጭ ቁጥር 2 ማከፋፈያ ጣቢያ በነባሩ የአርባ ምንጭ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የነበሩ የኃይል አቅርቦት ጫናዎችን ለማቃለል እንደሚያግዝም ገልፀዋል።
በማስፋፊያ ሥራው ከአርባ ምንጭ ቁጥር 2 – አርባ ምንጭ ቁጥር 1 የተዘረጋው ገቢ መስመር ራሱን የቻለ የፕሮቴክሽን ሥርዓት እንዳለው በመግለፅ ይህም ለሚያጋጥሙ የኃይል መቋረጥ ችግሮች በጣቢያው አቅም በወቅቱ መፍትሔ ለመስጠት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
በ1980ዎቹ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህ የማከፋፈያ ጣቢያ እያደገ ያለውን የኃይል ፍላጎት ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት የአቅም ማሳደግ እና ማስፋፊያ ሥራዎች የተከናወኑለት ሲሆን አሁን ላይ ሁለት ትራንስፎርመሮች፣ ስድስት ባለ 15 እና ሁለት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች አሉት።


