ማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ለኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

ማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ለኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

በወላይታ ሶዶ ከተማ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች አስተማማኝ ኃይል በማቅረብ ለኢንቨስትመንት መስፋፋትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የከተማዋ ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ቸርነት ተስፋዬ እንደገለጹት በከተማዋ ያሉት ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች በልበ ሙሉነት እንዲሰማሩ ዕድል ፈጥረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገልግሎት፣ በአምራች ኢንዱስትሪና በግብርና ዘርፎች 152 ኢንቨስትመንቶች ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ 41 ባለሀብቶች ደግሞ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በግንባታ ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም 29 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ለጽሕፈት ቤቱ መቅረባቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።

ይህ የኃይል አቅርቦት መሻሻል ከተማዋን የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ ለተያዘው ዕቅድ መሳካት መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን የገለጹት አቶ ቸርነት፤ በቀጣይም የሚመጣውን የኃይል ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአንጅድ ዱቄት ፋብሪካ የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ታደሰ በበኩላቸው ፋብሪካቸው ማሽኖቹን በአግባቡ የሚያንቀሳቅስ በቂ ኃይል እያገኘ በመሆኑን ምርታማነቱ ከመጨመሩ ባለፈ ፋብሪካው ለ70 ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር አስችሎታል ብለዋል።

መሰረተ ልማቶቹ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የወጣባቸው የሀገር ሀብቶች በመሆናቸው ሁሉም ሰው በባለቤትነት ስሜት ሊጠብቃቸው እንደሚገባ የሥራ ኃላፊዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top