ፕሮጀክቱ ከኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካዎች የሚመነጨውን ኤሌክትሪክ ለመጠቀም ያስችላል

ፕሮጀክቱ ከኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካዎች የሚመነጨውን ኤሌክትሪክ ለመጠቀም ያስችላል

የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ከኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካዎች ተረፈ ምርት የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለመጠቀም እንደሚያስችል የፕሮጀክቱ እና የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ የሥራ ኃላፊዎች አስታወቁ።

በፕሮጀክቱ የሳይት ሁለት ሥራ አስኪያጅ አቶ አርጋው ታዲ እንዳስታወቁት ከአምስቱ የኦሞ ስኳር ፋብሪካዎች ተረፈ ምርት የሚመነጨውን ከ180 ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ ከብሔራዊ የኃይል ቋት ጋር ለማገናኘት የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የግንባታ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

ይህም የታዳሽ ኃይል ስብጥርንና የማመንጨት አቅምን በማሳደግ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡

በኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ እና ሦስት ስኳር ፋብሪካዎች የቴክኒክ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ጡቃ በበኩላቸው ፋብሪካዎቹ የተፈጨውን የአገዳ ተረፈ ምርት ወደ ቦይለር በማስገባት ኃይል ያመነጫሉ።

በፋብሪካው ላይ የኃይል መቆጣጠሪያውን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከዚህ በፊት ዝግጁ መደረጋቸውን የተናገሩት አቶ ብርሃኑ ፕሮጀክቱ እንደተጠናቀቀ በፋብሪካው ላይ ምንም አይነት ተጨማሪ የግንባታ ሥራ ሳይከናወን ማገናኘት እንደሚያስችል አረጋግጠዋል።

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት ስኳር ፋብሪካ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል መላኩ ድጋፌ እንደተናገሩት ፋብሪካው ባሉት ሁለት ተርባይኖች 60 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ቢኖረውም እየተጠቀመበት ያለው ከ19 ሜጋ ዋት የማይበልጠውን እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቀ የሚመነጨውን ኤሌክትሪክ ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት በማስገባት የኃይል ብክነትን ለመቀነስ እና የፋብሪካውን ምርታማነት ለማሳደግ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

በፋብሪካዎቹ የሚመነጨው ኃይል ወደ ግሪዱ በሚገባበት ጊዜ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ስኳር ኮርፖሬሽን መካከል ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክረው የሥራ ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top