የአርባ ምንጭ ሁለተኛ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት የከተማዋን የኃይል አቅርቦት ያሳድጋል

የአርባ ምንጭ ሁለተኛ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት የከተማዋን የኃይል አቅርቦት ያሳድጋል

የአርባ ምንጭ ሁለተኛ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ ሥራ ሲጠናቀቅ የከተማዋን የኃይል አቅርቦት አሁን ካለበት ከአራት እጥፍ በላይ እንደሚያሳድገው የብሔራዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ደቡባዊ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አስታወቀ።

በፕሮጀክቱ የሳይት አንድ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዱዓለም መላኩ እንዳስታወቁት ፕሮጀክቱ በአርባ ምንጭ ከተማ አካባቢ ሊገነባ ለታሰበው የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንደስትሪ ፓርክ እና በ120 ኪሎ ሜትር ውስጥ ለሚገኙ አካባቢዎች አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ታስቦ እየተከናወነ ይገኛል።

የማከፋፈያ ጣቢያው ሁለት ባለ 125 ፣ ሁለት ባለ 63 እና ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ትራንስፎርመሮች የተከላና ገጠማ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን እና የአስር ባለ 33 እና አምስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ፓኔል የማስቀመጥ ሥራዎች እየተከናወነ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ አንዱዓለም ገለፃ የፕሮጀክቱ የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራ 65 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች 15 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን አጠቃላይ አፈፃፀሙ ደግሞ ከ62 በመቶ በላይ ደርሷል።

ከአርባምንጭ 2ኛ ማከፋፈያ ጣቢያ በተጨማሪ በወላይታ ሶዶ ሁለተኛ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ እየተከናወነ ያለው የማስፋፊያ ሥራ አጠቃላይ አፈፃፀሙ 62 በመቶ መድረሱን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

በማስፋፊያ ሥራው 250 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮችን የማስቀመጥ ሥራ እንደተከናወነ ገልፀው የሁለት ባለ 230 ኪሎ ቮልት ወጪ እና ገቢ መስመሮች የስቲል ስትራክቸር ተከላ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሆነም አስረድተበዋል፡፡

ለአርባ ምንጭ 2ኛ ማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ ሥራ ከ37 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ እንዲሁም ለወላይታ ሶዶ 2ኛ ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ሥራ ከ14 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በጀት ተይዞላቸዋል።

ከማከፋፈያ ጣቢያዎቹ በተጨማሪ ከወላይታ ሶዶ 2ኛ እስከ አርባ ምንጭ 2ኛ በሚዘረጋው የባለ 230 ኪሎ ቮልት ጥምር መስመር ላይ ከሚተከሉ 381 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች መካከል የ255ቱ የመሠረት ቁፋሮ ፣ የ242 የመሠረት ግንባታ እና የ22 ምሰሶዎች የተከላ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

የደቡባዊ ግሪድ ሳይት 1 የአንድ አዲስና የሁለት ነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎችን የማስፋፊያ ሥራ እንዲሁም የ216 ኪሎ ሜትር የባለ 230 እና 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ሥራዎችን ያካትታል።

የብሔራዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ደቡባዊ ማስፋፊያ ፕሮጀክት የግንባታ ሥራ ሃዮሰንግ ሄቪይ ኢንደስትሪስ ኮርፖሬሽን በተሰኘ የኮሪያ ኩባንያ በመከናወን ላይ ሲሆን የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀምም ከ60 በመቶ በላይ ደርሷል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top