የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ አፈፃፀም 35 በመቶ ደርሷል

የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ አፈፃፀም 35 በመቶ ደርሷል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደቡባዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የሽግዳን ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ አፈፃፀም ከ35 በመቶ በላይ መድረሱን በፕሮጀክቱ የሳይት 2 ሥራ አስኪያጅ ገለጹ፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ አርጋው ታዲ እንደገለጹት ሽግዳንና ቲርጋ ማከፋፈያ ጣቢያዎች እንዲሁም ከሳውላ እስከ ቲርጋ የሚዘረጋው የ196 ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ሥራ በሳይት ሁለት ስር የሚከናወኑ ናቸው።

ከ27 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ በጀት የተጀመረው የሽግዳን ማከፋፈያ ጣቢያ ሁለት ባለ 125፣ ሦስት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር ትራንስፎርመሮች እና ሁለት ሻንት ሪያክተሮች እንደሚኖሩት ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

ማከፋፈያ ጣቢያው አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ጥምር ገቢ መስመር፣ አንድ ባለ 132 እና አስራ አምስት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች እንደሚኖሩት ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

ሦስት ትራንስፎርመሮች፣ ሁለት ሸንት ሪያክተሮች፣ ብሬከሮችና ለማከፋፈያ ጣቢያው አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ዕቃዎች ሳይት መድረሳቸውንና ቀሪ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች በቅርቡ እንደሚገቡ አስታውቀዋል።

ከማከፋፈያ ጣቢያው በተጨማሪ ከሳውላ እስከ ሽግዳን በሚዘረጋው በባለ 230 ጥምር መስመር ላይ ከሚተከሉ 387 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች መካከል የ170ዎቹ የመሠረት ቁፋሮ፣ የ160 የመሠረት ግንባታ እና የ12 ምሰሶዎች የተከላ ሥራ መከናወኑን ገልፀዋል።

የማከፋፈያ ጣቢያው ሲጠናቀቅ በሰላማጎ ወረዳና በዙሪያው ለሚገኙ ቀበሌዎች እንዲሁም ለስኳር ፋብሪካዎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እንዲሁም የመስኖ ልማትን ጨምሮ በአካባቢው በሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸውን ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።

የፕሮጀክቱ የሲቪል መሃንዲስ አቶ መኮንን ጥላሁን በበኩላቸው የሠራተኞች መኖሪያ ቤት 20 በመቶ፣ የኃይል መቆጣጠሪያ ክፍሉ 40 በመቶ፣ የኬብል ማስተላለፊያ ቱቦዎች ሥራ 5 በመቶ እንዲሁም ጣቢያውን ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችሉ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት ሥራዎች 2 በመቶ መከናወኑን አስረድተዋል።

ከአምስት የትራንስፎርመርና ሁለት ሸንት ሪያክተር ማስቀመጫ የኮንክሪት መሠረት ሥራዎች መካከል የአምስቱ ሲጠናቀቅ የቀሪዎቹን በአንድ ወር ውስጥ በማጠናቀቅ ትራንስፎርመሮችን የማስቀመጥ ሥራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

እንደ አቶ መኮንን ገለፃ ከ452 የኤሌክትሮ ሜካኒካል ብረቶች መትከያ የኮንክሪት መሠረት ሥራ ውስጥ 300 የሚሆኑት መዘጋጀታቸውንና ቀሪዎቹን በሁለት ወራት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።

የግንባታ ሥራውን የሚያከናውነው የሃዮሰንግ ሄቪይ ኢንደስትሪስ ኮርፖሬሽን የሳይት ሁለት የግንባታ ሥራ አስከኪያጅ ሚስተር ዳንኤል ኪም የፕሮጀክቱ የግንባታ አፈፃፀም በጥሩ ሂደት ላይ ስለሚገኝ በተያዘለት የጊዜ ገደብና ጥራት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሽግዳንና ቲርጋ ጨምሮ አርባ ምንጭ 2ኛ ላይ የሚገነቡ ሦስት አዳዲስ ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ ነባሩ ወላይታ ሶዶ ሁለተኛ እና አርባምንጭ አንድ ላይ የሚከናወን የማስፋፊያ ሥራ እንዲሁም የ424 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ሥራዎችን ያጠቃልላል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top