የማከፋፈያ ጣቢያውን አቅም  ለመጠቀም እየተሠራ ነው

የማከፋፈያ ጣቢያውን አቅም  ለመጠቀም እየተሠራ ነው

የሞጆ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ያለውን የመሸከም አቅም ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን የጣቢያው ኃላፊ ገለፁ።

ኃላፊው አቶ ሚናስ ወንድምሞላ እንደገለፁት የማከፋፈያ ጣቢያው ከቢሾፍቱ ቁጥር 3 ማከፋፈያ ጣቢያ በ 230 ኪሎ ቮልት ኃይል ተቀብሎ  ለተለያዩ ከተሞችና ፋብሪካዎች ኃይል እያቀረበ ይገኛል።

ጣቢያው አስር ባለ 15 እና አራት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ቢኖሩትም አገልግሎት እየሠጡ የሚገኙት አራት ባለ 33 እና አራት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች ብቻ መሆናቸውን ኃላፊው  ገልፀዋል።

በ 33 ኪሎ ቮልት ባሉት ወጪ መስመሮች ለአንበሳ ቢራ ፋብሪካ፣ ለኢጀሬ ከተማ፣ ለአረርቲ ከተማና ሴራሚክ ፋብሪካ እንዲሁም በባለ 15 ኪሎ ቮልት መስመሮች ለሞጆና ቢሾፍቱ ከተሞች፣ ለአየር ኃይል እና በአካባቢው ለሚገኙ ቆዳ ፋብሪካዎች አስተማማኝ ኃይል እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።

ማከፋፈያ ጣቢያው አንድ ባለ 25 ሜጋ ቮልት አምፔር እና ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው  ትራንስፎርመሮች እንዳሉትም ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ሚናስ ገለፃ ሦስቱ ትራንስፎርመሮች 100 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም ቢኖራቸውም በአሁኑ ወቅት ለደንበኞች እየቀረበ ያለው ከ25 በመቶ የማይበልጠው ነው።

ማከፋፈያ ጣቢያው በአካባቢው ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት እንዳሳደገው የገለፁት ኃላፊው የጣቢያውን አቅም እና ዝግጁ የተደረጉ ሁሉንም ወጭ መስመሮች ጥቅም ላይ ለማዋል በአካባቢው ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ውይይት መደረጉን አንስተዋል።

ለአዳማ ከተማ ውሃ አገልግሎት፣ ለሞጆ ደረቅ ወደብ፣ ለሞጆ ከተማ እና በአካባቢ ለሚገኙ ዘጠኝ ፋብሪካዎች ተጨማሪ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችሉ የማሰራጫ መስመር ዝርጋታ በአገልግሎቱ በኩል መጀመሩን ገልፀዋል።

የሞጆ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top