በቢሾፍቱ ባለ 400 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ እየቀረቡ ያሉ ተጨማሪ የኃይል ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለፁ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ ሲሳይ አይቸው እንደተናገሩት የማከፋፈያ ጣቢያው ከገላን ማከፋፈያ ጣቢያ በባለ 400 ኪሎ ቮልት ጥምር መስመር ኃይል ተቀብሎ ለቢሾፍቱ፣ ዱከም ቁጥር 2 እና ለሞጆ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል ያከፋፍላል።
ማከፋፈያ ጣቢያው አገልግሎት መስጠት በጀመረበት ወቅት 100 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው ሁለት የ230/15 ኪሎ ቮልት ፓወር ትራንስፎርመሮች ብቻ እንደነበሩት የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ በአካባቢው በባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመር የኃይል ጥያቄ በመቅረቡ 100 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው ሁለት 230/33 ተጨማሪ ፓወር ትራንስፎርመሮች መተከላቸውን አስታውሰዋል።
በአቅም ማሳደግና ማስፋፊያ ሥራዎች በወቅቱ የነበረውን የኃይል ጥያቄ መመለስ ቢቻልም በአካባቢው ካለው የኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የኃይል ጥያቄው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ ያሉት የ400/230 አውቶ ትራንስፎርመሮች ተጨማሪ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም ቢኖራቸውም የአካባቢው የኃይል ፍላጎት በፍጥነት እየደገ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ ለማሳራጫ መስመሮች ኃይል የሚያቀርቡ ሁሉም የፓወር ትራንስፎርመሮች ተጨማሪ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም የላቸውም።
በዚህም ጣቢያው በ15 እና 33 ኪሎ ቮልት ካሉት 22 ወጭ መስመሮች ሁለቱ የ33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸውን ነው የገለፁት።
የኃይል ፍላጎቱ የጣቢያው ግንባታና የአቅም ማሳደግ ሥራዎች ሲከናወኑ ይመጣል ተብሎ ከታሰበው በላይ በፍጥነት እያደገ በመምጣቱ ተጨማሪ ጥያቄዎችን በወቅቱ ለመመለስ እንዳላስቻለ አቶ ሲሳይ ተናግረዋል።
ስለሆነም እያደገ የመጣውን የኃይል ጥያቄ በጊዜያዊነት ለመመለስ ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ ለማስቀመጥ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅትም ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያው የሚቀመጥበትን ቦታ የመለየትና ሌሎች የጥናት ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ነው ሥራ አስኪያጁ የጠቀሱት።
ከህብረተሰቡ እና ከኢንዱስትሪዎች እየቀረቡ ያሉ የኃይል ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመመለስ የሚያስችል የአቅም ማሳደግና የማስፋፊያ ሥራዎችን ለማከናወን ዕቅድ መያዙንም አብራርተዋል።
የቢሾፍቱ ቁጥር 3 ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ከሐምሌ 2012 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



