ፕሮጀክቱ ከመተግበሩ በፊት ጥናት መካሄዱ ተቀባይነቱ እንዲጎላ አድርጎታል

ፕሮጀክቱ ከመተግበሩ በፊት ጥናት መካሄዱ ተቀባይነቱ እንዲጎላ አድርጎታል

የአርባ ምንጭ 2ኛ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት የአካባቢያዊና ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ተፅእኖ ጥናት መከናወኑ ፕሮጀክቱ በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረጉ ተገለፀ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የካሳ ጉዳዮች አስተባባሪ አቶ ኢዘዲን ሸምሱ እንደገለፁት የፕሮጀክቱ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት በአካባቢው ሥነ ምህዳርና በማህበረሰቡ ላይ ሊፈጥር የሚችለው አወንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ እና ተፅዕኖዎችን እንዴት ማስቀረት እንደሚቻል ከዞን እስከ ቀበሌ ካሉ የመስተዳድር አካላት እና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

ግንባታው የሚካሄድበት ቦታ ለ140 ግለሰቦች ለቤት መስሪያነት በመመራቱና በውስጡም ስምንት መቃብሮች መኖራቸው በጥናቱ ስለተለየ ከዞን መስተዳደር፣  ቤት እንዲሰሩ ከተመሩ ግለሰቦች እና ከሟች ቤተሰቦች ጋር በመነጋገር መፍትሔ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የማስተላለፊያ መስመሩ ለማህበራዊ አገልግሎት በተሰጠ ቦታና በዞኑ አስተዳደር ህንፃ ላይ እንደሚያልፍ በጥናቱ በመረጋገጡ የሚዘረጋበት ቦታ እንዲቀየር መደረጉንም አቶ ኢዘዲን ጠቅሰዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ላይ የተካሄደው ጥናት በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ማረጋገጫ ተሰጥቶት እና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ወደ ትግበራ መገባቱንም ተናግረዋል፡፡

በፕሮጀክቱ ላይ ጥናትና ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት ሳይደረግ ወደ ሥራ ቢገባ ኖሮ በማህበረሰቡ ተቀባይነት ላያገኝ ይችል ነበር ያሉት አስተባባሪው ይህም በግንባታ ሥራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

በፕሮጀክቱ አማካሪ ባዮሰን ፓወር ኩባንያ የአርባ ምንጭ 2ኛ ማከፋፈያ ጣቢያ የአካባቢና ማህበረሰባዊ ጉዳዮች እንዲሁም የጤናና የሥራ ላይ ደህንነት ባለሙያ አቶ ቤካን ዳምጠው በበኩላቸው ሥራ ተቋራጩ አካባቢውን የማይበክሉ ማሽነሪዎች እንዲጠቀም እና ለፕሮጀክቱ ግንባታ የዋሉ የተለያዩ ተረፈ ምርቶች በአግባቡ እንዲወገዱ ክትትል እየተደረገ ስለመሆኑም ገልፀዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top