የሪጅኑን የበጀት ዓመት ዕቅድ ለማሳካት ሁሉም መረባረብ አለበት

የሪጅኑን የበጀት ዓመት ዕቅድ ለማሳካት ሁሉም መረባረብ አለበት

በሪጅኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የነበሩ ክፍተቶችን በማረም በቀሪ ወራት የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምስራቅ ሪጅን አንድ ዳይሬክተር አሳሰቡ፡፡

ሪጅኑ በስሩ የሚገኙ የማከፋፈያ ጣቢያ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኦፕሬሽንና የጥገና ባለሙያዎች በተገኙበት የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በድሬድዋ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡

የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ወርዲ ሙሐመድ እንደገለፁት ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ግምገማ የሪጅኑን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የተወሰዱ የመፍትሄ ርምጃዎች ላይ ውይይት በማድረግ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነው፡፡

ሁሉም የሪጅኑ አመራርና ሠራተኛ በተቋሙ እየተከናወነ ያለውን የሪፎርም ሥራ በሚደግፍ መልኩ የኦፕሬሽን ሥራዎችን በአግባቡ ማከናወን እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

በግምገማው በተለያየ ጊዜ በችግር መልክ ሲነሱ የቆዩና መፍትሄ ያላገኙ ጉዳዮችን በመለየት በቀጣይ በሚፈቱበት አግባብ ዙሪያም አቅጣጫ እንደሚቀመጥ አመልክተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ሪጅኑ ያቀዳቸውን ተግባራት በሙሉ ለማከናወን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያልተከናወኑ ተግባራትንና በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ለማከናወን የታቀዱ ሥራዎችን በማካተት የመቶ ቀን ዕቅድ መዘጋጀቱን የጠቆሙት አቶ ወርዲ አመራሩና ሠራተኛው በዕቅዱ ላይ የጋራ መግባባት ኖሯቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ውይይት እንደሚደረግበትም አብራርተዋል።

የሪጅኑ የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም በድሬደዋ ቁጥር ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያ የኦፕሬተር ባለሙያ አቶ በሱፍቃድ ባዩ ቀርቧል፡፡

አስተማማኝና ያልተቆራረጠ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር በሪጅኑ ሥር ባሉ የማከፋፍያ ጣቢያዎችና ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ጊዜውን የጠበቀ የቅድመ መከላከል፣ የትንበያ፣ የፍተሻ ጥገና ሥራዎች እንዲሁም የማዘመን ሥራዎች በራስ አቅም ጭምር መከናወናቸው በሪፖርቱ በጥንካሬ ተነስቷል፡፡

የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት እና የማስተላለፊያ መስመሮች በቀለበት አለመያያዛቸው በክፍተት የተጠቀሰ ሲሆን በቀረበው ሪፖርት ላይ በተሳታፊዎቹ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል፡፡

የምስራቅ ሪጅን አንድ በስሩ ዘጠኝ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን እና 1950 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ማስተላለፊያ መስመሮችን ያስተዳድራል፡፡

ግምገማው በነገው ዕለትም የሚቀጥል ይሆናል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top