በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኮምቦልቻ 2 ወደ ኮምቦልቻ 1 ማከፋፈያ ጣቢያ በተዘረጋው ባለ 132 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ላይ ስርቆት የፈፀሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በደቡብ ወሎ ዞን የቃሉ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
የተፈፀመው ስርቆት ለአንድ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶ መውደቅና በኮምቦልቻ፣ በደሴ አቀስታ እና ዓለም ከተሞች እና አካባቢያቸው ለመብራት መቋረጥ ምክንያት ሆኖ ነነበር፡፡
በስርቆቱ የተሳተፉ አራት ግለሰቦችን ማለትም ሁለቱ በስርቆቱ በቀጥታ የተሳተፉ፣ አንድ ገዥ እና ቀሪው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ የገለፀው ፖሊስ ፅ/ቤቱ ምርመራውን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለፍርድ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀም ስርቆት የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን በመረዳት በመሰል ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አካልት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም ፖሊስ አሳስቧል፡፡
በቀጣይም በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀም ስርቆትን ለመከላከል ከማህበረሰቡና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ገልጿል፡፡
የኢነርጂ አዋጅ 810/2006 አንቀጽ 26 በኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ ወይም ማከፋፈያ ተቋማት ላይ ጉዳት ያደረሰ ማንኛውም ሰው ከ5 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም እስከ 50 ሺህ ብር በሚደርስ ገንዘብ ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”