በማከፋፈያ ጣቢያዎች ስዊች ጊሮች ወይም መቆጣጠሪያዎች እርጅናና ብልሽት የተነሳ የሚከሰቱ የኃይል መቆራረጦችን ለማስቀረት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ሁለት ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ አስታወቀ፡፡
በመምሪያው የማከፋፈያ ጣቢዎች የኦፕሬሽንና ጥገና የሥራ ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ አሻግሬ እንዳስታወቁት በሪጅኑ የነበሩት የማከፋፈያ ጣቢያ መቆጣጠሪያዎች በአየር የሚሰሩና ረጅም ጊዜ ያገለገሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ተደጋጋሚ ብልሽት ያጋጥማቸው ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ብሬከሮቹ ለብናኝና ለእርጥበት ተጋላጭ በመሆናቸው ለብልሽት እንደሚዳረጉ እና ሲበላሹም አውቶክሎዠር በሚባል የመቆጣጠሪያ ዘዴ ለደንበኞች ኃይል የሚደርስበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት ከፍተኛ ቮልት ሲመጣ የሚከሰቱ ችግሮችን ጠግኖ ወደ ኦፕሬሽን ለመመለስ ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ እና ቀደም ሲል የነበረው አውቶክሎዠር ከመቆጣጠሪያ ፓናሉ ተነጥሎ በውጭ የሚገኝ በመሆኑ በኃይል አቅርቦቱ ላይ መስተጓጎል ሲፈጥር ቆይቷል፡፡
የሚያጋጥሙችግሮችን በመቅረፍ ለደንበኞች ያልተቆራረጠ ኃይል ለማቅረብ ስዊች ጊሮችን የማዘመን ሥራ እየተከናወነ ስለመሆኑም አቶ አበበ አስታውቀዋል፡፡
በሪጅኑከሚገኙ ስምንት ማከፋፈያ ጣቢያዎች መካከል የሶዶ 1 እና የሆሳዕና ባላ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመር ስዊች ጊሮች በጂአይ ኤስ ብሬከር ተቀይረው አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው በደንበኞችይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችንና ቅሬታዎችን እንደፈታ አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የሶዶ 1 ባለ 15 ኪሎ ቮልት እንዲሁም የሳውላ እና ቀይ አፈር ማከፋፈያ ጣቢያዎች የ33 ኪሎ ቮልት ስዊች ጊር ቅየራ በመከናወን ላይ ይገኛል ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፡፡
እንደአቶ አበበ ገለፃ የጂ አይ ኤስ ስዊች ጊሮቹ በጋዝ የሚሰሩ እንዲሁም ከእርጥበትና ብናኝ ነፃ በመሆናቸው የመበላሸት ዕድላቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ለደንበኞች ያልተቆራረጠ ኃይል ለማቅረብ ያስችላሉ፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



